banner

መርጌታ ነን በማለት 827 ሺህ ብር ያጭበረበሩት ወንድማማቾች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

​#FastMereja I ሰኔ 28 ቀን 2018 ዓ.ም.

​በምስራቅ ጎጃም ዞን ሉማሜ ከተማ “መርጌታ ስመኘው የባህል መድኃኒት” በሚል የሐሰት ስም በመጠቀም፣ ከአንድ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ላይ 827 ሺህ ብር ያጭበረበሩ ስመኝ አባትነህ እና ያዛቸው አባትነህ የተባሉ ወንድማማቾች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የከተማዋ ፖሊስ አስታወቀ።

​የሉማሜ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት አዛዥ ኢንስፔክተር በድሉ መልሰው እንደገለጹት፣ አካሉ መለሰ የተባለው ተበዳይ በቡና ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ ሲሆን፣ ቡና ያስረከበው ደንበኛ ገንዘቡን ሊመልስለት ባለመቻሉ ለችግር ተዳርጎ ነበር። ተጠርጣሪዎቹ ወንድማማቾች ይህንን አጋጣሚ በመጠቀምና የሐሰት ሰነድ በማዘጋጀት “መርጌታ ነን፤ ያልተመለሰልህን ገንዘብ በባህል መድኃኒትና በጸሎት እናስመልሳለን” በሚል ማታለል የጠቀሱትን ከፍተኛ ገንዘብ ተቀብለዋል።

​ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ባደረገው ተከታታይ ክትትል በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ሲሆን፣ የተጭበረበረው 827 ሺህ ብር በከተማ አስተዳደሩ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት በጊዜያዊነት በኤግዚቢትነት እንዲቀመጥ ተደርጓል። በአሁኑ ወቅት በአጭበርባሪዎቹ ላይ ሕጋዊና ተገቢው ቅጣት እንዲያገኙ የምርመራ መዝገብ ተደራጅቶ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

​በሉማሜ ከተማ ተመሳሳይ የማጭበርበር ወንጀሎች እየተደጋገሙ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም 625 ሺህ ብር በሐሰት ያጭበረበረ ሌላ ግለሰብ በ2 ዓመት ከ9 ወር ፅኑ እስራት መቀጣቱ ይታወሳል። ማኅበረሰቡ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለጠፉ መሰል የተጋነኑና የሐሰት ማስታወቂያዎችን በመለየት ራሱን ከትልቅ የገንዘብ ኪሳራና ማጭበርበር እንዲጠብቅ ፖሊስና የፋስት መረጃ ዝግጅት ክፍል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

#ችሎት

Leave a Comment