#FastMereja I አዋሽ ኢንሹራንስ በ2018 በጀት ዓመት ከ6.1 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ የአረቦን ገቢ (GWP) በመሰብሰብ የ35 በመቶ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቡንና በግሉ የመድን ዘርፍ የገበያ መሪነቱን በይፋ ማስቀጠሉን አስታወቀ። ኩባንያው በሁሉም ዋና ዋና የሥራ ዘርፎቹ ዓመታዊ ግቡን የተሻገረ ጠንካራ አፈጻጸም ያሳየ ሲሆን፣ በተለይም በሕይወትና ጤና እንዲሁም በተካፉል ኢንሹራንስ ዘርፎች በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ቀዳሚ ሥፍራ አጠናክሮ መጓዙ ተገልጿል።
የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ገመዳ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የተመዘገበው አስደናቂ ውጤት ተቋሙ የተከተለው ጠንካራ ስትራቴጂ፣ በሳል አመራርና የሰው ኃይል ቁርጠኝነት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል። ኩባንያው ያቀዳቸውን ግቦች በላቀ ሁኔታ ማሳካቱ ዓላማውን ወደ ተጨባጭ ውጤት የመቀየር አቅሙን እንደሚያሳይ የጠቆሙት ሰብሳቢው፣ ለዚህ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ደንበኞችና ባለአክሲዮኖች ምስጋና አቅርበዋል።
የአዋሽ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጅባት አለምነህ ፋጂ በበኩላቸው፣ ስኬቱ ከሠራተኞች፣ ደንበኞች፣ ባለአክሲዮኖች፣ የሽያጭ ወኪሎችና ብሮከሮች ጋር የተደረገ የጠንካራ ትብብር ፍሬ መሆኑን አብራርተዋል። በአዲሱ የሥራ ዓመት የገበያ መሪነቱን ይበልጥ ለማጠናከር በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የላቀ የደንበኛ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እንደሚሠራ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸው፣ ኩባንያው ወደፊትም ተደራሽ የኢንሹራንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ ለኢትዮጵያ የመድን ዘርፍ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
#ቢዝነስ ዘገባ




