banner

ማይ ሲድ አካዳሚ አዲስ የዲጂታል ትምህርት መተግበሪያ ይፋ ሊያደርግ ነው።

​#FastMereja I ማይ ሲድ አካዳሚ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እና የዲጂታል ትምህርት ተዳራሽነትን ለማስፋፋት አዲስ የትምህርት አፕሊኬሽን በቀጣይ ሳምንት በይፋ ወደ ሥራ እንደሚያስገባ አስታወቀ። ተቋሙ ሀገራዊ የትምህርት ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የያዘውን ራዕይ ዕውን ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጻል።

ዛሬ አርብ ነሐሴ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ​ይህ አዲሱ የትምህርት ፕላትፎርም ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች የታሰበ ሲሆን፣ በሀገሪቱ አዲስ የትምህርት ሥርዓተ-ትምህርት (Curriculum) መሠረት የተቀረጸ ነው። ተማሪዎች ትምህርታቸውን በብቁ መምህራን በተዘጋጁ የቪዲዮ እና የጽሑፍ ማብራሪያዎች ምቹ በሆነ የኦንላይን መተግበሪያ አማካኝነት በቀላሉ መከታተል የሚያስችላቸው እንደሆነ ተመልክቷል።

​ተቋሙ የትምህርት ይዘቶችን በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በሶማሊኛ፣ በዓፋርኛ እና በትግርኛ ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ ያቀደ ሲሆን፣ በዚሁ የመጀመሪያ ምዕራፍ በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጁ የቪዲዮ ትምህርቶች ለተጠቃሚዎች ክፍት ይደረጋሉ። ይህ አዲስ አፕሊኬሽን ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ለሕዝብ አገልግሎት እንደሚለቀቅ ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ትምህርቶቹን ለማግኘት በቴሌብር የክፍያ ስርዓት የተመቻቸ መሆኑ ተነግሯል። #ሳይ_ቴክ





Leave a Comment