banner

የ6ኛው ግራንድ አፍሪካን ረን በመጪዉ ኦክቶበር በዋሽንግተን ዲሲ ሊካሄድ ነው።

6ኛው ግራንድ አፍሪካን ረን በፈረንጆቹ አቆጣጠር በመጪዉ ኦክቶበር 12/ 2024 ወይም ጥቅምት 2/ 2017 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ ሊካሄድ መሆኑን ዛሬ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገለፀ። ‘አብሮነት መሻል ነው’ በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ዝግጅት፤ ኢትዮጵያዊያንን ብሎም አፍሪካዊያንን ማሰባሰብ፣ የመጀመሪያው ትውልድ ልጆችን ከባህላቸው ጋር የበለጠ ማቀራረብ፣ እና ለተለያዩ በጎ ስራዎች ገቢ ማሰባሰብን ዓላማው አድርጎ የሚከናወን ነው። በዚህ ዝግጅት፥ በሺህ የሚቆጠሩ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት የሚሳተፉበት መሆኑ ተገልፆ፣ በዝግጅቱ ለመሳተፍ ምዝገባው በአዘጋጆቹ ዌብሳይት www.africanrun.com ላይ መጀመሩ ታውቋል።

የዝግጅቱ ቀዳሚ ኣጋር የሆነው አሌክሳንድሪያ ቶዮታ ለተሳታፊዎች የመኪና ሽልማት ማዘጋጀቱም ተገልፆል። “ሁሉም አሸናፊ ነው” በሚል መርህ በተዘጋጀው በዚህ ሽልማት የዝግጅቱ ተሳታፊዎች አንደኛም ሆነ መጨረሻ ሆነው ርቀቱን ቢያጠናቅቁም ሁሉም ተሳታፊ መኪናውን የማሸነፍ እኩል ዕድል እንደሚኖረው ታውቋል። በዝግጅቱ ቀን የሩጫው ማጠቃለያ ላይ የሎተሪ ዕጣ የማውጣት ስነ ስርዓት ተከናውኖ የመኪናው አሸናፊ በይፋ ለታዳሚዎች የሚገለጽ መሆኑ ተመልክቷል።

በዘንድሮው ዝግጅት በክብር እንግድነት ተሳታፊዎችን ለማበረታታት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ በሴቶች የማራቶን የዓለም ሪከርድ ባለቤት አትሌት ትግስት አሰፋ፣ እና በሴቶች የ5ሺ የዓለም ሪከርድ ባለቤት አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ በዝግጅቱ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል። አትሌት ደራርቱ ቱሉ ከመጀመሪያው ጀመሮ ዝግጅቱን በመደገፍ እና በማበረታታት ያገዘች መሆኗን ጠቁማ፣ “አገራችንን በዓለም መድረክ በመልካም ገፅታ እንድንታዋወቅ ያደረገው የአትሌቲክስ ስፖርት በዉጭ ለሚገኙ ወገኖቻችን የመሰባሰቢያ መድረክ ሆኖ ማገልገሉ ዝግጅቱን ልዩ ያደረገዋል” ብላለች። አያይዛም፣ ዝግጅቱ ማህበረሰባችን የተለየ ቦታ የሚሰጠውን የአትሌቲክስ ስፖርት በመጠቀም አብሮነትን ማጎልበት ያስችላል ስትል ገልፃለች።

የማራቶን ሪከርድ ባለቤቷ አትሌት ትግስት አሰፋ በበኩሏ ዝግጅቱ ላይ ተገኝታ ተሳታፊዎችን እንደምታበረታታ ገልፃ፣ ወገኖቻችን ተሰባስበው በአንድነት የሚያሳልፉባቸው መድረኮች ሁሉ የአብሮነታችን መገለጫዎች ናቸው ስትል ገልፃለች። የ5ሺ ሪከርድ ባለቤቷ አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ እንዲሁ ወገኖቿን በቦታው በመገኘት እንደምታበረታታ ገልፃ፣ አገራቸውን ወክለው በኦሎምፒክ መድረክ ለሚሳተፉ አትሌቶች ሁሉ መልካም ምኞቷን አስተላልፋለች።

የውድድሩ ዋና አዘጋጅ የሆኑት ዶክተር ጋሻው አብዛ ዝግጅቱ ከአንድ ቀን የ5 ኪ.ሜ የቤተሰብ ሩጫነት የበለጠ ፋይዳ ያለው መርሀግብር መሆኑን ጠቁመዉ፤ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያንን በማቀራርብ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል። ዝግጅቱን ለቀጣይ አራት ዓመታት በቀዳሚ ስፖንሰርነት እንደሚደግፍ በቅርቡ ያስታወቀው የአሌክሳንደሪያ ቶዮታ ጄኔራል ሴልስ ማኔጀር አቶ ያሬድ ማን አለብህ እንደገለጹትም አፍሪካዊያን በተለይ ኢትዮጵያዊያን የአሌክሳንደሪያ ቶዮታ የረጅም ዓመታት ደንበኞች በመሆናቸው በግራንድ አፍሪካ ረን በኩል ደንበኞቻቸውን ለማመስገን እና ለመደገፍ እንደወሰኑ አመልክተው፣ ማህበረሰቡ የተለየ ቦታ የሚሰጠውን የአትሌቲክስ ስፖርት በመጠቀም ዝግጅቱ አብሮነትን ማጎልበት የሚያስችል እንደሆነም አበክረው ገልጸዋል።

በተመሳሳይም፣ የዝግጅቱ የረጅም ጊዜ አጋር የሆነው የዳሸን ባንክ የስትራተጂ ዋና ኦፊሰር፣ አቶ ኤሊያስ ሁሴን ባስተላለፉት መልዕክት የዳያስፖራው ማህበረሰብ ዳሸን ባንክ ካሉት ቀዳሚ ደንበኞች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመው፣ እንደ ግራንድ አፍሪካን ረን ያሉ ኢትዮጵያዊያንን የሚያሰባስቡ ዝግጅቶችን በቀጣይነት በመደገፍ ለዳያስፖራው ማህበረሰብ አጋርነቱን የሚገልፅበት አንዱ አጋጣሚ እንደሆነ ገልፀዋል። በተያያዘም፣፣ በፈጣን እድገቱ በሰሜን አሜሪካ አንዱ የኢትዮጵያዊያን የስኬት ተምሳሌ እየሆኑ የመጡት የሮሚንግ ሮስተር ባላቤቶች፣ ግራድን አፍሪካን ረንን ለሶስተኛ ጊዜ እየደገፉ እንደሆነ ጠቁመው፣ በቀጣይነትም ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

ግራንድ አፍሪካ ረን በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በሁለተኛው ቅዳሜ በዋሽንግተን ዲሲ የሚካሄድ ብዙሃኑን የሚያሳትፍ ዓመታዊ የ5ኪሜ የጎዳና ላይ የመዝናኛ ሩጫ ነው። የዘንድሮው ዝግጅት ለ6ኛ ጊዜ የሚዘጋጅ ይሆናል። ባለፉት አምስት ግራንድ አፍሪካ ረን ዝግጅቶች፣ የአገራችን ብርቅዬ አትሌቶች ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ስለሺ ስህን፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ በላይነህ ደንሳሞ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ቁጥሬ ዱለቻ እና ሌሎችም በክብር እንግድነት ተገኝተዉበታል።

Leave a Comment