#FastMereja I በከፍተኛ የሕክምና ባለሙያዎች ጥምረት የተመሰረተውና በ1.2 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባው “ዶክተርስ አላያንስ ጀኔራል ሆስፒታል” በዛሬው ዕለት የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ተመረቀ።
ሆስፒታሉን በክብር እንግድነት ተገኝተው የመረቁት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ናቸው። በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የሆስፒታሉ መስራቾች፣ የሕክምና ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ሆስፒታሉ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ እና “ከወረቀት ነፃ” (Paperless) በሆነ አሰራር የሚመራ ሲሆን፣ ይህም የሕመምተኞችን መረጃ በዘመናዊ መንገድ ለመያዝ እና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ያስችለዋል። ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ባለ 100 አልጋ ሆስፒታል ሆኖ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በጠቅላላው 1.2 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ይህ ግዙፍ የጤና ተቋም፣ በአሁኑ ወቅት ለ100 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ግን እስከ 300 ለሚደርሱ ባለሙያዎች የሥራ ዕድል እንደሚሰጥ ታውቋል።
ሆስፒታሉ ሕክምና ከመስጠት ባሻገር የማህበረሰቡን የጤና ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚሰራም አስታውቋል።
ዶክተርስ አላያንስ ጀኔራል ሆስፒታል በኢትዮጵያ የሕክምና ዘርፍ ውስጥ በባለሙያዎች ጥምረት ተመስርተው ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ከፈሰሰባቸው ጥቂት ተቋማት መካከል አንዱ በመሆን በዛሬው ዕለት በይፋ ወደ ሥራ ተቀላቅሏል።
#ጤና




