banner

አራት ሽልማት የወሰደችው ተማሪ የምስራች ምትኩ በዲላ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ አዲስ ታሪክ ጻፈች

#FastMereja I በዲላ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የዘንድሮ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ፣አንድ ስም ከመድረኩ ጎልቶ አስተጋባ—የምስራች ምትኩ በባችለር ዲግሪ መርሃ-ግብር ትምህርቷን የተከታተለችው ይህች ብርቱ ተማሪ፣ማንም ያልጠበቀውን እና በኮሌጁ ታሪክ እጅግ አነጋጋሪ የሆነ ደማቅ ድል አስመዝግባለች።

የምስራች ያስመዘገበችው ስኬት ተራ አልነበረም የአሸናፊዎች አሸናፊ የሚያሰኛትን አራት ታላላቅ የክብር ሽልማቶች በአንድ መድረክ ጠራርጋ ወስዳለች።

በዕለቱ የክብር ሞገስ የሆነችው የምስራች ከክፍሏ 1ኛ በመውጣት የመጀመሪያዋን የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልማለች፣ከዲፓርትመንቷ 1ኛ በመሆን ልህቀቷን አጠናክራ ሁለተኛዋን የወርቅ ሜዳሊያ በአንገቷ ላይ አጥልቃለች፣ከአጠቃላይ የዲግሪ መርሃ-ግብሩ 1ኛ በመሆን ከሁሉም ተማሪዎች ልቃ በመገኘት የክብር ዋንጫን ወደ ላይ ከፍ አድርጋለች።

በመጨረሻ ከአጠቃላይ ሴት ተማሪዎች 1ኛ በመውጣት የሴቶችን አቅምና ጥንካሬ በተግባር በማስመስከር ሁለተኛዋን የክብር ዋንጫ በድል አነሳች።

ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን እና ሁለት የክብር ዋንጫዎችን በአንድ ጊዜ የወሰደችው የምስራች ለሌሎች ተማሪዎች በተለይም ለሴት እህቶቿ ትልቅ የብርታት ምንጭ እና ህያው አርአያ ሆና አልፋለች።ይህ አይነቱ የተደራረበ ስኬት በትምህርት ጥራትና በግል ጥረት የሚመጣ እንጂ በአጋጣሚ የሚገኝ አለመሆኑን የዕለቱ ታዳሚዎች በሞቀ ጭብጨባ መስክረውላታል።

ዘገባው፦ የዳራሮ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ነው #ማህበራዊ

Leave a Comment