ላለፉት ሁለት ዓመታት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የአገልግሎት ዘመናቸውን አጠናቀው ወደ ሃገር ቤት መጠራታቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ አስታወቀ።
ይህንንም ተከትሎ በዋሽንግተን ዲሲ የሽኝት ፕሮግራም ተደርጎላቸዋል ብሏል። በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ስለሺ በቀለ ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም በርካታ ኢትዮጵያዊያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን አደረጃጀቶች እና ተቋማት አመራር አባላት በተገኙበት የሚስዮኑን ያለፉትን ሁለት ዓመታት የስራ እንቅስቃሴ ሪፖርት ማቅረባቸውን ኤምባሲው አስታውቋል።

በሪፖርታቸዉም ሚሲዮኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት መንግስት የሰጠዉን ተልዕኮ በብቃት መወጣቱን ገልፀው የተሰሩ ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶችን በዝርዝር አቅርበዋል ብሏል።
በዚህም በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ ዉጤቶች መመዝገቡን በማንሳት ለእነዚህ ተግባራት ስኬታማ መሆን ዳያስፖራዉ ያበረከተዉ አስተዋጽዖ “ተኪ የሌለዉ” እና “ከፍተኛ ነበር” ሲሉ መግለጻቸውን እና ዳያስፖራዉ ለሀገሩ እያበረከተ ላለዉ አስተዋጽዖም ምስጋና ማቅረባቸውን መረጃው አካቷል።
በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ የታደሙት በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸውም አምባሰደሩ በቆይታቸው ሃገራቸውን በመወከል ላሳዩት አመራር ምስጋና ማቅረባቸውን ኤምባሳዊ ገልጿል።

በኤምባሲ የሚሰሩ ዲፕሎማቶች እና ሰራተኞች የስራ ጊዜአቸውን አጠናቀው ለሚመለሱት አምባሳደር ዶ/ር ስለሺ በቀለ እና ለምክትል የሚሲዮን መሪ አምባሳደር ዘላለም ብርሃን አሸኛኘት እንዳደረጉላቸው ከኤምባሲው በማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።