#FastMereja
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያቀረቡት ጥሪ ሶስተኛ ምዕራፍን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት የመጡ ወጣቶች የሚሳተፉባቸው በርካታ ሁነቶች በመዘጋጀት ላይ እንዳለ ተገለፀ።
ዛሬ ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት በፅ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከጷጉሜ 3-5/2016 ዓ.ም በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የሚካሄደው ጉዞ ወደ ሀገር ቤት የክረምት ፌስቲቫል በቀደሙት ሁለት ዙሮች በተከናወኑ ጥሪዎች ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንን ከሀገራቸው ባህልና ታሪክ ጋር የሚያስተዋውቁ ሁነቶች እንደተዘጋጁ ነው የተገለጸው።
በሁነቶቹ አማካኝነትም ወጣቶቹ ከሀገራቸው ጋር ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ትስስር እንዲፈጥሩ እንዲሁም የሀገር ፍቅር ስሜታቸው እንዲዳብር የሚያደርጉ ዕድሎች እንደተፈጠረላቸው ተገልጿል።
በዚህም ወደመጡባቸው ሀገራት ሲመለሱ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረግ እንደተቻለ ነው የተነገረው።
አሻራዎን ያኑሩ፤ የዕረፍት ጊዜዎን ያጣጥሙ በሚል መሪ መልዕክት በመከናው ላይ ባለው ሶስተኛ ምዕራፍ በመሳተፍ ላይ ያሉ ወጣቶችም የዕረፍት ጊዜያቸውን ተጠቅመው በልዩ ልዩ የበጎ አድራጎትና የአካባቢ ጥበቃ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ፣ የቱሪስት መስህቦችን በመጎብኘትም ስለሀገራቸው ታሪክና ባህል ተጨማሪ ዕውቀት እንዲጨብጡ ለማድረግ በመሰራት ላይ ይገኛል ተብሏል።
በዚህ ፌስቲቫል ላይ ታዋቂዎቹ ጆኒ ራጋ እና ራስ ጆኒ ከመሐሪ ብራዘርስ ባንድ ጋር የሙዚቃ ኮንሰርት የሚያቀርቡ ሲሆን በተጨማሪም የብሔረ ብሔረሰቦች የባህል ትሪኢት፣ ፋሽን ሾው ወዘተ በርካታ ሀገርን የሚያስተዋውቁና የሚያዝናኑ ዝግጅቶች ተካተዋል፡፡
በሁነቶቹ ላይ የሚሳተፉ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንም ትስስራቸውን የሚያጠናከሩበትና ሀገራቸውን ይበልጥ የሚያውቁበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር ነው የተነገረው።





1 comment
ነሐሴ 3 ማለት ለሚቀጥለው አመት ነው