#FastMereja
ተከሳሽ ረመዳን አብራር ወንጀሉን የፈፀመው በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው አሮጌ ፖስታ ቤት ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነው።
በአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የፒያሳ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል መርማሪ ዋና ሳጅን ማሪሞ ቀባቶ እንደገለፁት የግል ተበዳይ ወይዘሪት አመዘነች አስፋው በሞባይል ስልኳ እያወራች ሳለ ተከሳሽ ረመዳን አብራር ስልኩን በመንጠቅ ዘሎ ቱቦ ውስጥ ይገባል።
የግል ተበዳይ ያሰማችውን የይድረሱልኝ ጥሪ ተከትሎ በወንጀል መከላከል ስራ ላይ የነበሩ የፖሊስ አባላት ወንጀል ፈጻሚው እንዳያመልጥ ባደረጉት ወንጀል ፈፃሚውን በቁጥጥር ስር እንዳዋሉት የጉዳዩ መርማሪ ሳጅን ማሪሞ ቀባቶ ጨምረው ገልፀዋል።
ፖሊስ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማደራጀት በአቃቤ ህግ በኩል ክስ የተመሰረተበት መሆኑን የገለፁት መርማሪው ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ አምስተኛ ወንጀል ችሎት በተከሳሽ ረመዳን አብራር ላይ የ2 ዓመት ከ8 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ማስተላለፉን ተናግረዋል።
የወንጀል መከላከል አባላቱ ወንጀለኛውን ለመያዝ የፈጸሙት ተግባር ለሌሎች አባላት ጥሩ ምሳሌ መሆኑን መርማሪው ተናግረው መሰል ወንጀል ፈፃሚዎች በመጠቆም ህብረተሰቡ ተባባሪ እንዲሆን መርማሪው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
