banner

«እጅግ ለዛገና ለተንቀርፈፈና ለሙስና ተጋላጭ ለሆነ አገልግሎት ዋጋ ጭማሪ ማድረግ ሕዝብን ማስመረር ነው።»

የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሙሼ ሰሙ

ሰሞኑን እያወዛገበ ያለው የመንግስታዊ ተቋማት የአገልግሎት ተመን ጭማሪ ከመንስኤው ጀምሮ ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር የማይጣጣምና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሚያስደነግጥ እየሆነ ነው።

በብቸኝነት ያለ ተወዳዳሪ አገልግሎት ሰጭ ስለሆኑ ብቻ በቂ፣ አሳማኝ ምክንያት ሳይኖር እጅግ ለዛገና ለተንቀርፈፈና ለሙስና ተጋላጭ ለሆነ አገልግሎት ከ150% እስከ 700 % ጭማሪ ማድረግ ሕዝብን ከማስመረር ውጭ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም። የዚህ ዓይነቱ መብትና ስልጣን ከምን እንደሚመነጭ ለመረዳትም አዳጋች ነው።

የመንጃ ፈቃድ እድሳት፣ የተሽከርካሪ ባለቤትነት ማረጋገጫ (ሊብሬ)፣ መንጃ ፈቃድ ለጠፋበትና ለቦሎ ወዘተ የሚሰጠው አገልግሎት ካርድ፣ ወረቀትና ተለጣፊ አትሞ ከመስጠት ውጭ የቴክኒክ፣ የብቃት ወይም የእውቀትና የክህሎት አገልግሎት የለውም። የጭማሪው መንስኤም አልተገለጸም። አዲሱ የኢኮኖሚ ፓሊሲ ያሰሸከተለው የእቃ ዋጋ መናር፣ የደሞዝ ጭማሪውን በራስ ገቢ መሸፈን ወይስ ሌላ ?

የወረቀቱም ሆነ የካርዱ ወይም የተለጣፊው ጥሬ እቃ ለማስመጣትም ሆነ ከገበያ ለመግዛት ዋጋው ከ10 ብር አይበልጥም። ኮምፒዩተር ከፍቶ ስም አጣርቶና ነባሩ መንጃ ፈቃድ ሕጋዊ መሆኑን አረጋግጦ ካርድ አትሞ ለመስጠት (ተጓዳኝ ወጭ ጨምሮ) 100 ብር ለማያወጣ አገልግሎት 900% ትርፍ መጠየቅ ምንም ዓይነት አመክንየ ሊቀርብበት አይችልም ።

የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል በተመጣጣኝ ዋጋ ለማገልገል የተቋቋሙ ናቸው። ከመርሆዎቻቸውም ውስጥ ተደራሽነት፣ ቀልጣፋ፣ ለተመጣጣኝ አገልግሎት ተመጣጣኝ ዋጋ መጠየቅ ዋነኞቹ ናቸው ።

ከተሽከርካሪ ጋር የተያያዘ አገልግሎት ወረቀት፣ ካርድና ተለጣፊ ከማተምና የጽሕፈት አገልግሎት ከመስጠት ያለፈ ትርጉም ያለው ስራ አይጠይቅም። ልክ እንደ ሸቀጥ ነጋዴ በዘፈቀደና እጥረት ስለተፈጠረ ወይም ብቸኛ አገልግሎት ሰጭና አቅራቢ ስለሆነ የፈለጉትን ዋጋ መቆለል ምን ታመጣላችሁ መሆን አለበት። በቸኛ አረጋጋጭ መሆን ንጉስ መሆን ማለት አይደለም።

ተሽርካሪ ያለው ሁሉ አቅም አለው ማለት አይደለም። በዚህ ጣራ በነካ ኑሮ ዋጋ መቆለል የእለት ጉርሳቸው ከዚህ አገልግሎት ጋር የተያያዘ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች መርሳት ነው። እንደዚህ ዓይነት የዘፈቀደ የዋጋ ጭማሪ በነጋዴውም ሆነ በሹፌሩ ዘንድ ሊቀሰቅስና ሊያቀጣጥል የሚችለውን የዋጋ ጭማሪ ማጤን መልካም ነው። አንተ ዋጋ አትጨምር እኔ ግን እንደልቤ ዋጋ እጨምራለሁ ማለት ውጤቱ በገዛ ራስ እግር ላይ ጥይት የመተኮስ ያህል ነው።

10 comments

Addisu Hussen September 30, 2024 - 5:57 am

ችግሩ ዋጋ መጨመሩ ብቻ አይደለም እኛም ችግሩን እንደ ጸጋ መቀበላችን እና ችግሩን ያመጣብን ሰዉ መሆኑን እረስተን ከፈጣሪ እንደሆነ ማመናችን እና መቀበላችን ነው ለዚህ ሁሉ ችግር ያጋለጠን!

Reply
ዝም በል እስኪ September 30, 2024 - 6:00 am

ዋናው ፍላጎታቸው መማረራችን ነው የነሱ ግብ ይሀው ነው።

Reply
Fetiya Anwar Yesuf September 30, 2024 - 6:06 am

ዋጋው እና አጨማመሩ ጭራሽ አይገናኝም አሁንስ ደሀውን ያማከለ ኑሮ ራሱ ሊጠፋ እኮ ችግር ነው ነገሩ ሁሉ

Reply
Bereket Markos September 30, 2024 - 6:18 am

በሁሉ ነገር ዋጋ ጭማሪ የሚባለውን ነገር አሁንማ እያስመረረ መጥቷል።

Reply
Sadam Nuru September 30, 2024 - 6:19 am

አንድ ወቅት ጌታቸዉ እረዳ ያለዉ አለ ዩቲቨ ላይ አብይ ያለ ጦርነት እያደናገ ካልሆነ ሀገር እንደ ሀገር ማስቀጠል አይችልም።

Reply
Gebby G Max September 30, 2024 - 6:25 am

እኔ ልጨምር አንቴ ግን አትጨምር በዶላር እና በተለያዩ የመንግስት አገልግሎት ላይ ያየነው የመንግስት ተግባር ነው
ለምሳሌ የመብራት ዋጋ መጨመር የውሃ ዋጋ መጨመር የትራንስፖርት ዋጋ መጨመር የብሌን ታርፍ ዋጋ መጨመር የታክሲ ዋጋ መጨመር እድያውም ኢትዮ ቴለኮም የመጨመር እቅድ ይዟል እና እኼ የዋጋ ጭማሪ እና የኑሮ ውድነት ከግብ የማድረስ እቅድ እስከ መቼ እንደሆነ አናውቅም

Reply
Anteneh Mesfin September 30, 2024 - 6:28 am

የመንግስታዊ አገልግሎቶች ሁሉም የማይቀመሱ ሆነዋል

Reply
Solomon Asefa September 30, 2024 - 6:44 am

ነጋዴው አደብ ገዝቶ ህዝቡን አክብሮ ሲነግድ መንግስት ተብዬው ገበያው ኢኮኖሚው የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ እና እንዳይረጋጋ በማረግ ጉልህ ድርሻ እየተወጣ ነው ያሳዝናል በጣም ውጤቱ ጥሩ እንደማይሆን ግልፅ ነው

Reply
Berhanu Ganebo September 30, 2024 - 6:55 am

ኃላፊነት የጎደለው መንግስት !

Reply
Michel Beza September 30, 2024 - 7:10 am

እጅግ ክፋ አረመኔ የዜጎቹ ጉዳይ ግድ የማይሰጠው ግዴለሽ እራስ ወዳድ መንግስት ነው ግድ የለም ይሄ የመረረው ህዝብ የተነሳ እለት መመለሻምየለው

Reply

Leave a Comment