ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በዐራቱም ሃይማኖቶች በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የመምህር የማርያምወርቅ ተሻገር ሁለተኛ መጽሐፍ በዛሬው እለት በግዮን ሆቴል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣ የእስልምና ፣ የካቶሊክ ፣ የወንጌላውያን ህብረት አባቶች ፣ ዘማርያን ፣ አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በድምቀት ተመርቋል።
መጽሐፉ በዋነኝነት በአራቱ ሃይማኖቶች ማለትም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፣ በእስልምና ፣ በካቶሊክ ፣ በወንጌላውያን አማኞች እና ኢትዮጵያዊነት ላይ ትኩረት አድርጎ የተዘጋጀ መጽሐፍ ሲሆን፣ አብሮነት እና ሰላምን፣ ሃይማኖት ሀገርን እንዴት እንደሚያቆም ፣ ሃይማኖቶች ያላቸውን የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ፣ የተለያዩ አስተምህሮዎች በክፍል በክፍል ተሰናድተው የቀረቡበት መጽሐፍ ነው።
የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጥናታዊ ጽሑፉን ወደ መጽሐፍ የቀየረው የመምህር የማርያምወርቅ ተሻገር ከ1983 ዓ.ም እስከ 2013 ዓ.ም ባሉት 30 አመታት ውስጥ በሃይማኖት ተቋማቱ ከተለቀቁ መዝሙሮች ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ በእስልምና፣ በካቶሊክና ወንጌላውያን ሃይማኖቶች የመዝሙር (መንዙማ) ግጥሞች ውስጥ የቀረቡበትን መንገድ የሚያሳይ ነው።
በመጽሐፍ ምርቃት መርሐግብሩ ላይ ከአራቱም የሀይማኖት ተቋማት የተወከሉ በመጽሐፍ ላይ የዳሰሳ ጥናት የቀረበ ሲሆን የየሃይማኖቱ ተቋማት በመወከል ስለ ሀገር የተዘመሩ ዝማሬዎችን (መንዙማ) ለታዳሚያን ቀርቧል።
መጽሐፉ “ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የቆመችባቸውን የጋራ ምሶሶዎች ከመዝሙሮቹ ግጥሞች ነቅሶ አውጥቶ በመተንተን፣ እንደሀገር የገጠመንን ስብራት ለመጠገንና ልዩነቶችን ለማጥበብ የተገለጠ የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው” ተብሏል።
መምህር የማርያምወርቅ ተሻገር ተወልዶ ያደገው ጎንደር አዞዞ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪውን በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ጽሑፍ (B.A) አግኝቷል፡፡ በዲላ ዩኒቨርሲቲ በፒጂዲቲ የማስተማር ስነዘዴ ዲኘሎማ ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ጽሑፍ
ሁለተኛ ዲግሪውን ፣ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በሰነ መለኮት የመጀመሪያ ዲግሪ እና በአልፋ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪውን ተከታትሏል፡፡
“ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት” መጽሐፍ ጸሐፊ የሆነው መምህር የማርያምወርቅ ተሻገር በአሁኑ ወቅት የሎዛ ሚዲያ እና ኢቨንት መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ እና ከዚህ ቀደም በብዙዎች ዘንድ የተወደደውን ወድቆ የተገኘውን መጽሐፍ ደራሲ ሲሆን በዛሬው እለት የተመረቀው መጽሐፍ መታሰቢያነቱ ለአባቱ አቶ አሻግሬ አቸነፍ እና ለእናቱ እማሆይ ታክላ አየለ እንዲሆን አበርክቷል።
መጽሐፉ ከነገ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም መጽሐፍት ቤቶች የሚከፋፈል መሆኑን በምረቃው መርሐግብር ላይ ተገልጿል።




