በእንሰሳት ሃብት ልማት እና የእንስሳት ተዋጽዖ ምርቶች ላይ ትኩረት ያደረገው በኢትዮጵያ ቀዳሚው የእንስሳት ዘርፍ አውድርዕይ እና ጉባኤ ሊካሄድ ነው።
#FastMereja I 13ኛው የኢትዮ ፖልተሪ ኤከስፖ (ኢትዮፔከስ)፣ 9ኛው የአፍሪካ እንስሳት ዓውደርዕይና ጉባዔ (አሌክ) እንዲሁም 4ኛው የአፒካልቸር እና አኳካልቸር ኢትዮጵያ ዓለምዓቀፍ የንግድ ትርዒትና ዘንድሮ የሚጀመረው የባዮ ኢነርጂ የንግድ ትርዒት ጥራት ያላቸውን የዘርፉ ዋነኛ አንቀሳቃሾች በማሳተፍ ከጥቅምት ከ21 እስከ 23/ 2017 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ዛሬ በስካይላይት ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል።
ከ14 ሃገራት የተውጣጡ ከ100 በላይ ዓለምዓቀፍ የእንስሳት ሃብት ዘርፍ ተዋናዮች እና ስመጥር የሀገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት፣ ከዘርፉ ባለሙያዎች እና የንግድ ጎብኚዎች ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት ዓውደርዕይ እና ጉባዔዎች ለዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ እና ስጋ፡ ንዑስ ዘርፎች ዕድገትና ልማት ከፍተኛ አስተዋፅአ አበርክተዋል። እነዚህ ኹነቶች የዘርፉ ባለሙያዎች እና የንግዱ ማህበረሰብ ትልቁ መሰባሰቢያ በመሆናቸው የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣ የእውቀት ሽግግርን በማምጣት እንዲሁም የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስተዋወቅ ለዘርፉ ልማት ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማረጋገጥ መቻላቸውን የፕራና ኢቨንትስ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬከተር አቶ ነብዩ ለማ ተናግረዋል።
ለ3 ቀናት በሚካሄደው ዓውደ ርዕይና ጉባዔ አጠቃላይ የእሴት ሰንሰለቱን የሚወክሉ መሰረታቸውን በቻይና፣ ቼከ ሪፐብሊክ፡ ኢትዮጵያ፣ ፈረንሳይ፡ ጀርመን፣ ህንድ፤ ኬኒያ፡ ጆርዳን፡ ኔዘርላንድሰ፣ ስኮትላንድ፡ ቶጎ፡ ቱርክ፣ ዩጋንዳ እና አሜሪካ ያደረጉ ዓለም ዓቀፍ የዘርፉ መሪዎች እና ጠንካራ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ከንግድ ጎብኚዎች ጋር ጠንካራ የስራ ግንኙነት ለመፍጠር ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል ተብሏል። በኹነቱ ከ5000 በላይ የኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ እና አለም አቀፍ ሀገራት ጎብኚዎች ይጠበቃሉ።
ፕራና ኢቨንትስ ዘርፈ ብዙ የንግድ ትርዒት እና የቢዝነስ ኹነቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በማዘጋጀት እና በማማከር ስራ ላይ የተሰማራ እና ዘርፉን በእውቀት በቴክኖሎጂ እና በግብዓቶች ለመደገፍ ዓለማ አድርጎ የተቋቋመ ኃ/የተ/የግ/ማ ነው፡፡




