በምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ አስተዳዳር ነዋሪ እና የምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን የሆኑትን ረዳት ኢንስፔክተር ጀሚላ ቢንዳ የተባለችው ባለቤቱ ላይ የግድያ ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ በእስራት ተቀጥቷል።
ሟች በምዕራብ አርሲ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በከፍተኛ አመራርነት ሲሰሩ ቆይተዋል ። በፖሊስ ሙያ እያገለገሉ ባሉበት ወቅት ከአቶ ከድር ጅቦ ከተባለ የዶዶላ ከተማ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ጽ/ቤት ሰራተኛ ጋር ትዳር መስርተው ይኖሩ እንደነበር ተገልጿል ።
ጥንዶቹ በትዳር ከ30 ዓመት በላይ በመቆየት የአምስት ሴት ልጆች እና የአንድ ወንድ ልጅ ማፍራት ችለው እንደነበር የዶዶላ ከተማ አስተዳደር የፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አብዱላዚዝ ጀማል ተናግረዋል።
ሟች በስራቸው ላይ ባሳዩት ብርታት አዋሽ ማሰልጠኛ ገብተው በመሰልጠን የረዳት ኢንስፔክተርንት ማዕረግ በማግኘት የሴቶች እና ህጻናት ክፍል ኃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ በነበረበት ሰዓት በትዳራቸው ላይ አለመግባባት እየተፈጠረ በሽምግልና ለመፍታት ሲሞከር የነበረ ቢሆንም ለልጆች ሲባል ትዳር ሳንበትን አብረን እንኖራለን በሚል ተስማምተው እንደነበረ ተነግሯል።
ሚያዚያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ረዳት ኢንስፔክተር ጀሚላ ስራ ውለው ደክሟቸው ለማረፍ ገብተው ይተኛሉ። አቶ ከድር ከጓደኞቻቸው ጋር መጠጥ ጠጥተው አምሽተው ወደ ቤት ሲገባ ሁሉም የቤተሰቡ አባል መተኛታቸው ያረጋግጣል ።
ባል አልጋ ለይቶ ስለነበር ሚስት ማንም ወደ እኔ ክፍል የሚገባ የለም በማለት በሩን ሳይዘጉ ነበር የተኙት ይሁን እና መተኛታቸውን ካረጋገጠ በኋላ የእንጨት መፍለጫ መጥረቢያ ዛቢያ እንጨት አንስቶ በእንቅልፍ ላይ ያለችውን ባለቤቱን አንገቷን እና ጭንቅላቷን በመምታት ከባድ ጉዳት አድርሷባታል ።
ጉዳት ካደረሰባት በኋላ ተሸክሞ ወደ ጤና ተቋም ካደረሳቸው በኋላ ከአካባቢው ይሰወራል ይሁን እና በህክምና እርዳታ ላይ የነበሩት ኢንስፔክተር ጀሚላ ህይወት ያልፋል።ይህንን ድርጊት ተከትሎ የኦሮሚያ ፖሊስ መምሪያ እና የምዕራብ አርሲ ዞን ፖሊስ መምሪያ አመራር አካላት በአባሏ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ መኮንኗ ሚያዚያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ወዳጅ ዘመድ እና የስራ ባልደረቦች ባሉበት ስርዓተ ቀብሯ መፈጸሙ ገልጿል ።
ፖሊስም ባለቤቱን የገደለውን ግለሰብ በማፈላለግ ክትትል ሲያደርግበት ከቆየ በኋላ ከ12 ቀናት ቆይታ በኋላ ከተሸሸገበት በምዕራብ አርሲ ዞን ገደብ አሳሳ ወረዳ ሚያዚያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም በአንድ ግለሰብ ቤት ተሸሽጎ በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉ ፖሊስ ገልጿል ።
በዚህም ባለቤቱን ማለትም ረዳት ኢንስፔክተር ጀሚላ በተኙበት ጉዳት አድርሶ ህይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉ በማመን ድርጊቱን የፈጸመው በሌላ ሰው ስለምትጠረጥረኝ ነው በማለት ቃሉን ለፖሊስ ይሰጣል። ፖሊስ መዝገቡን በማጠናከር ለዓቃቢ ህግ ይልካል ። ዓቃቢህግ በከባድ የሰው መግደል ወንጀል ክስ በመመስረት ለምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይልካል ።
ፍርድ ቤትም ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ታህሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት በ18 ዓመት እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት ሲሆን ተከሳሹን ሸሽጎ ያስቀመጠው ግለሰብ ደግሞ 5ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ መወሰኑን የዶዶላ ከተማ አስተዳደር የፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አብዱላዚዝ ጀማል ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል


3 comments
ለምን ገደላት??
😭
መታወቂያ ካላደስክ እሙሙ አልሰጥም ብላው ነው😏