banner

#ከክብሮች ሁሉ የሚበልጠውን ክብር የመረጠው ሕጻን

“ወደ እግዚአብሔር መንግስት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” የሚል ድንቅ ኃይለ ቃል በሐዋርያት ሥራ 14:21 ሰፍሮ እናገኛለን፡፡

ይህን ቃል መነሻ አድርገውም ሰመዕታት ከአላውያን ነገስታት፣ ከአላውያን መኳንንት ዘንድ ስለ ሚያገኛቸው መከራ ሳይፈሩ ስለ ክርስቶስ አምላክነት መስክረው የክብር አክሊል ተቀዳጅተዋል፡፡ ከእነዚህ ሰማዕታት አንዱ ገና በሶስት ዓመቱ ሰማዕትነትን የተቀበለው ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ናቸው፡፡

ቅድስት ኢየሉጣ የሮም ግዛት በሆነው አንጌቤን በሚባል ሀገር በክርስትና ሃይማኖት በበጎ ምግባር፣ በፈሪሃ እግዚአብሔር ጸንታ ትኖር የነበረች ደግ ሴት ነበርች፡፡ ልጇ ቅዱስ ቂርቆስንም በስርዓት ነበር ያሳደገችው፡፡

በዘመኑ የነበረውን አረማዊ አስተዳዳሪ እለእስክንድሮስን በመፍራት ከልጇ ጋር ከሮም ወደ ተርሴስ ብትሰደድም መኰንኑ እነርሱ የሚገኙበት ሀገር ገብቶ ክርስቲያኖችን እያሳደደ መግደል ጀመረ፡፡ የንጉሡ ወታደሮችም እግዚአብሔርን እንዲክዱ፣ ለጣዖት እንዲሰግዱ ቅድስት ኢየሉጣንና ቅዱስ ቂርቆስን አስፈራሯቸው፡፡ ቅዱሳኑ ግን በክሕደት ለመወሰድ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

በዚህም ምክንያት ጽኑ መከራ አደረሱባቸው፡፡ በጋሉ ብረቶች በመቸንከርና መላ ሰውነታቸውን በመብሳት፣ በዓይንና በአፍንጫቸው ውስጥ ጨውና ሰናፍጭ በመጨመር አሰቃዩዋቸው፡፡ በዚህ ሁሉ መከራቸው ውስጥ ግን አምላካችን እግዚአብሔር ስቃያቸው እንዳይሰማቸው ያጸናቸው ነበር፡፡

በሌላ ጊዜም ንጉሱ ጸጉራቸውን ከነቆዳቸው በመላጨት በእሳት አቃጠላቸው፡፡ ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስም ገና በሶስት ዓመቱ የሚደርስበትን ይህን መከራ በእግዚአብሔር ቸርነት ተቋቁሞ ከእናቱ ጋር በተጋድሎው ቀጠለ፡፡

ሰውነታቸውን ከላይ እስከ ታች በችንካር ሲቸነክሯቸው ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ገብርኤል አዳናቸው፣ በመጋዝ ሰንጥቀው በብረት ምጣድ ሲቆሏቸው እግዚአብሔር ከሞት አስነሳቸውና ዳግም በገዢዎች ፊት ቆመው ስለ ክብሩ መሰከሩ፡፡ በዚህ የተበሳጨው ንጉስም በፍጹም ተአምራት መኮንኑ ያደረገውን ጫማ ወደ በሬነት የቀየረውን ቅዱስ ሕጻን ምላሱን አስቆረጠው፡፡ እግዚአብሔር ግን በቸርነቱ አድኖለታል፡፡

በመጨረሻም በፈላ ውሃ የተሞላ ትልቅ ጋን ውስጥ ሊጨምራቸው ሲዘጋጁ እናቱ ቅስት ኢየሉጣ ፈራች፡፡ ይሁንና ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስ “እናቴ ሆይ አትፍሪ ሶስቱን ሕጻናት ያደነ አምላክ ያድነናል” እያለ ያጽናናት ነበር፡፡ በዚህ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ እቶኑን ወደ ቀዝቃዛ ውሃ ቀይሮታል፡፡ ከዚህ በኋላም ብዙ ዓለማዊ ክብር እንደሚሰጧቸው ቃል ቢገቡላቸውም፣ ከክብሮች ሁሉ የሚበልጠውን የመንግስተ ሰማያት ክብር በመምረጥ በብዙ ተጋድሎና በጽኑ መከራ ውስጥ ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ቆይተው ጥር 15 ቀን በመንፈቀ ሌሊት አንገታቸውን ተቈርጠው በሰማዕትነት አርፈዋል፡፡

ዓለምን ንቀዋት የእግዚአብሔርን መንግስት አስቀድመዋል፡፡ ዛሬም በየገዳማቱ ዓለምን ንቀው የሚኖሩ መነኮሳትና ገዳማውያን በጸሎታቸው ኃይል ያደርጋሉ፡፡ ገዳማቸውን እናግዝ በዓታቸውን እናጽና፡፡

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444



2 comments

Pedro Rodrigez Kelile January 23, 2025 - 9:52 am

“ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።”
— 2ኛ ዮሐንስ 1፥9

Reply
Abdisa Etana January 23, 2025 - 9:53 am

ኢየሱስ ክርስቶስ እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፣ ነገር ግን የማእዘን ራስ የሆነ ድንጋይ ነው። በሌላ በማንም ድነት የለም፤ ልንድንበት የሚገባ በሰዎች መካከል የተሰጠ ሌላ ስም ከሰማይ በታች የለምና።
የሐዋርያት ሥራ 4:11-12

Reply

Leave a Comment