በተፈጥሮ በታደለችው ድንቅ ውበት ላይ በስጋዊ ውበት ይበልጥ ጎልታ ለመታየት የምትጥር፣ ሁልጊዜ ከነጭ ሐር የተሠራ ልብስ የምትለብስ፣ ከሽቱ ሁሉ ይልቅ የሚበልጥ ውድ ሽቱን የምትቀባ፣ በወርቅ የምታጌጥ፣ በክፉ የዝሙት ወጥመድ በርካቶችን ለማጥመድ የምትጥር፣ በክፋት ሥራዋ ሁሉ ጸንታ የምትኖር ሴት ነበረች፡፡ ጠላት ዲያብሎስም የዚህን ዓለም ጣዕም አጣፈጠላት፡፡ ማርያም እንተ ዕፍረት፣ ባለሽቱዋ ሴት፡፡ አንድ ቀን እንደልማዷ ነጭ ሐር ለብሳ፣ አጊጣና ተኳኩላ ፊቷን በመስታወት አይታ ግሩም መዓዛ ያለው ሽቱ ተቀባች፡፡ ፊቷን በመስታወት በማየት ለአንድ ሰዓት ያህል የጉንጯ ቅላትና ደም ግባት፤ የዓይኗ ወገግታና ጥራት ማማሩን በማየት አደነቀች፡፡ በዚህ ቅጽበት ግን በጎ ኀሳብ በአእምሮዋ መጣ፤ ያም ሞት የማይቀርላት መሆኑ ነበር፡፡
መንፈስ ቅዱስ ወደ አእምሮዋ ማስተዋል መለሳት፡፡ “ይህን ሁሉ ታስወግድ ዘንድ መልኬንም ትለውጥ ዘንድ ሞት ትመጣ የለምን? ይህ መልካም ሽታ ወደ ትልነትና ወደ መሽተት ይለወጣል፡፡ ይህስ ብርታት ፍጻሜው ጉስቁልናና ድካም አይለምን? ሊቀርቡኝ የሚወዱትስ የሚርቁኝ አይደሉምን? የዚህን ዓለም ገንዘብ ብገዛ፣ ብነዳ ሰውነቴን ከድካም ዐይኖቼንም እንባ ከማፍሰስ የሚያድንልኝ ይኖራልን? ወይስ ይህ ሁሉ ከሞት ያድነኝ ዘንድ ይችላልን? እያለች ራሷን መመርመር ጀመረች፡፡ ሰው ሁሉ እንደሚጸየፋት ስታስብ ደግሞ ይበልጥ ፈራች፡፡ በዚያን ዘመን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን እንደሚቀበልና ኃጢአትን እንደሚያስተሰርይ ሲወራ የሰማችው ትዝ ሲላት ገንዘቧን ሰብስባ የከበረውን የአልባስጥሮስ ሽቱ ገዛችበት፡፡
በፈሪሳዊው በስምዖን ቤት በእንግድነት እንደተቀመጠ ሰማች፡፡ ስትሄድ ደጆቹ ተከፍተው ነበር፡፡ ብዙ ሕዝብ ቢኖርም በዝሙት የምትኖር ነበረችና እንዳትነካቸው ገለል ብለው አሳለፏት፡፡ ያለማፈር ገብታ ጌታችንም በስምዖን ቤት እንደ ግብፃውያን አቀማመጥ እግሩን ወደኋላ አድርጎ ነበር፤ አንድም ወንበሩ እንደ አፍርንጆች ወንበር እግር ወደኋላ የሚያደርግ እርሷም ከአጠገቡ ስትደርስ ከእግሩ በታች ከሰገደች በኋላ ‹‹በስተኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታብስ ጀመር፤ በራስ ጠጉሯም ታብሰው፣ እግሩንም ትስመው፣ ሽቱም ትቀባው ነበር፡፡ በቤቱ ያስተናገደው ስምኦን ግን በልቡ “ይህስ ነቢይ ቢሆን ኖሮ ይህቺ የምትዳስሰው ሴት ኃጢአተኛ እንደሆነች ያውቅ ነበር” አለው፡፡
ጌታችንም ስምዖን ያሰበውን ሁሉ አውቋልና፤ “እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ÷ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብክልኝም፤ ይህች ሴት ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች፤ በጠጉርዋ አበሰች፡፡ አንተ አልሳምከኝም፤ እርስዋ ግን ከገባች ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም፡፡ አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች፡፤ ስለዚህ እልሃለሁ÷ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል፡፡ እርስዋንም ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል፤ አምነትሽም አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት፡፡ እውነት እላችኋለሁ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለእርሷ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል ክብሯን የገለጸላትና ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት የደመራት ቅድስት ናት፡፡
ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391
ወይም
አቢሲኒያ ባንክ
141029444
የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444


1 comment
ፋኖን ሰላም በልልኝ