banner

የስልኩን ባትሪ አይኔ ላይ አብርተሃል በሚል የግድያ ወንጀል የፈፀመዉን ግለሰብ በእስራት ተቀጣ።

#FastMereja I የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመዉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በካፋ ዞን ጨና ወረዳ ዉስጥ ነዉ። የወንጀል ድርጊቱን ፈፃሚ ተከሳሹ ጥላሁን አሰፋ ይባላል። የጨና ወረዳ ፖሊስ በምርመራዉ እንዳረጋገጠዉ ተከሳሹ በጨና ወረዳ በላ ሻሻ ቀበሌ ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 1:30 ሰዓት ገበያ ዉሎ ወደ መኖሪያ ቤቱ በመመለስ ላይ እያለ የግል ተበዳይም ምሽቱን ወደቤቱ እየተመለሰ በወቅቱ ጨለማ ስለነበር የእጅ ሞባይሉን ተከሳሽ አይን ላይ ያበራበታል።

ተከሳሹ ለምን አይኔ ላይ ታበራለህ በሚል በተፈጠረ ፀብ ተከሳሽ የግል ተበዳይን በጩቤ አንገቱ አከባቢ አንድ ጊዜ በመውጋት ህይወቱ እንዲያልፍ ማድረጉን በካፋ ዞን ፍትህ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ዐቃቤ ህግ መላኩ መንገሻ ተናግረዋል።

እንደ ዐቃቤ ህግ መላኩ ገለፃ ሟችም ገዳይም በወቅቱ መጠጥ ጠጥተዉ እንደነበርና በስካር መንፈስ ውስጥ ሆኖ የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙን በፖሊስ በሰጠዉ እምነት ቃል መረጋገጡን አስረድተዋል።

የጨና ወረዳ ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር አድርጎ የምርመራ መዝገቡን በሰዉና በህክምና ማስረጃ በማደራጀት ክስ እንዲመሰረትበት የምርመራ መዝገቡ ለዞኑ ዐቃቤ ህግ እንደላከ ዐቃቤ ህጉ ገልፀዋል።

የካፋ ዞን ዐቃቤ ህግ ከጨና ወረዳ ፖሊስ የደረሰውን የምርመራ መዝገብ መነሻ በማድረግ ግለሰቡን የኢ.ፌ.ዲ .ሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 540 ላይ የተደነገገውን በመተላለፋ በፈፀመው የግድያ ወንጀል ክስ መስርቶበት ካፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ማቅረቡን ዐቃቤ ህጉ አስረድተዋል።

የካፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ህግ ግለሰቡ ላይ የመሰረተዉን የክስ መዝገብ ግራ ቀኙን አዳምጦ ግለሰቡን ጥፋተኛ ነዉ በማለት የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል።

በዚሁ መሰረት የካፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ባስቻለው የወንጀል ችሎት ተከሳሽ ጥላሁን አሰፋ በ12 ዓመት እስራት እንዲቀጣ ዉሳኔ አስተላልፎበታል ሲል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኔኬሽን ዘግቧል።

#ችሎት

1 comment

Šf Šøló Öne July 20, 2025 - 4:59 pm

xender kefitehal blo megdelm tejemiroal

Reply

Leave a Comment