#FastMereja I የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የዩኒቨርሲቲውን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 100ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ- በዓል አንዱ አካል የሆነው ዩኒቨርሲቲውና ከተማውን የሚያስተሳስሩ እሴቶችን የሚያወሱ ልዩ ዝግጅቶች የሚቀርቡበት መርሃ-ግብር ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ በመሆን ዛሬ ሐምሌ 17/2017 ዓ.ም እየካሄደ ይገኛል።
“የከተማችን ቀን” በተሰኘው በዚህ መርሃ ግብር በክብር እንግድነት የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚንስትር አቶ መላኩ አለበል 70 አመታት የትምህርት፣ የስኬት፣ የእውቀት ጊዜ እንደነበር አንስተው መጪው አመታት ከዚህ የላቀ ጉዞ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኛው በበኩላቸው ጎንደር ከተማን ወደ ቀድሞ ገናናነት ለመመለስ እየተሰራ ነው ብለው የከተማው ህዝብ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የባለቤትነት ስሜት አለው ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አጽደወይን (ዶ/ር) ጎንደር የሁላችንም ከተማ እንደሆነችው ሁሉ ሁላችንም ተባብረን ልናለማትና ሲንከባለሉ የመጡ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ልንመልስላት ይገባል ብለዋል።
ከዚህ በላቀ ለልጆቻችን የተመቸች እንድትሆን የማድረጉ ጥረት ለይደር የሚባል የቤት ሥራ አይደለም ከመንግሥት፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም ላይ ከተበተኑ ልጆቿ እና ወዳጆቿ፣ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሁሉ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ብለዋል።
ለጎንደር ከተማ ሁለገብ እድገትና ልማት ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ የቀረበ ሲሆን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ ጎንደር ከተማ እንደሌላው የቱሪዝም ዘርፍ በሜዲካል ቱሪዝም፣ በኮንፈረንስ ቱሪዝም፣ በትምህርትና በኢንቨስትመንት የምትታወቅ ከተማ እንድትሆን የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ እንደሆኑ አስራት አጽደወይን (ዶ/ር) ገልጿል።
“የከተማችን ቀን” በቋሚነት በየዓመቱ እንዲከበር ከንቲባው ጥያቄ አቅርበዋል።
የጎንደርና የሀገር ባለውለታዎች ለሆኑት የምስጋና እውቅና ሽልማት ለግለሰቦች እና ተቋማት ተበርክቷል።




