#FastMereja I በኢትዮጵያ የትያትር ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ30 የአለም ሀገራት መድረኮች የሚታይ “ወደ ማዶ” አለም አቀፍ የትያትር ጉዞ ሊጀመር መሆኑን ዛሬ በሸራተን ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል።
አንጋፋ ተዋንያን የሚተውኑበት “ወደ ማዶ” የተሰኘው ትያትር በውጭ ሃገር መድረክ ይመረቃል የተባለ ሲሆን በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ ታላላቅ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፤ የጥበብ ወዳጅ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በነሐሴ ወር በአፍሪካ የተለያዩ ሃገራት ይደረጋል ተብሏል።
በቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ተደርሶ በሴም እማኑኤል የተዘጋጀው “ወደ ማዶ” ትያትር የኮሜዲ ዘውግ ያለው ማህበራዊ ጉዳዮችን እያነሳ የሚሄድ፣ ሲሆን በሕይወታችን የሚገጥሙን ችግሮች ለማውጣት የሚደረግን ትንቅንቅ የሚያሳይ ነው። በትያትሩ ላይ በትወና ብቃቷ ከፍተኛ የተመልካች ፍቅርና አድናቆት ያላት ሃረገወይን አሰፋን ጨምሮ ሽዋፈራው ደሳለኝ እና የኋላእሸት ዘሪሁን ይተውኑብታል ተብሏል።
“ወደ ማዶ” አለም አቀፍ የትያትር ጉዞ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚገኙባቸው በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ አህጉራት በሚገኙ ሀገራት እንዲሁም በኢትዮጵያ ከ30 በላይ መድረኮች እንደሚታይ ተገልጿል። በተጨማሪም እስካሁን ባልተለመደ መልኩ ትያትሩ በሚታይባቸው ሀገራትና መድረኮች ከትያትሩ ጎን ለጎን ለየኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የገቢ ማሰባሰቢያ ይደረጋል የተባለ ሲሆን ይህንንም በጎ አላማ ለማሳካት ከማዕከሉ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።




