#FastMereja I “ጉብዝና ያሸልማል” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለው የ2017 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የሒሳብ ትምህርት የመዝጊያ ውድድር ነሀሴ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚሊኒየም አዳራሽ ይከናወናል።
ዛሬ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጲያ ብቸኛው የሆነው የሒሳብ ትምህርት አወዳዳሪ ተቋም ማይሶሮባን ኢትዮጵያ ኃ/የተ/የግ/ ማህበር ከአንድ ደቂቃ ጋር በመሆን፤ ሀገር አቀፍ የትምህርት እና የስሌት ውድድር በሀገራችን በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች መዘጋጀቱን ገልጿል።
ውድድሩ የሚከናወነው ከ3 እስከ 12ተኛ ክፍል ድረስ ሲሆን፤ ተማሪዎቹ የሚፈተኑበት ቋንቋ መንግስት ባዘጋጀው መማሪያ መፀሀፍ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቁሟል።
ስድስት ዙሮች ያሉት ውድድሩ ፤ አምስቱ ዙሮች በየከተሞቹ የተከናወኑ ሲሆን የመጨረሻው እና የስድስተኛው ዙር የፍፃሜ ውድድር፤ የየከተማው አሸናፊ ተማሪዎች በተገኙበት ከሀምሌ 28 እስከ ነሀሴ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው፤ በሚሊኒየም አዳራሽ ይወዳደራሉ ተብሏል።
የአሸናፊዎች አሸናፊ ተማሪዎች ተለይተው ለአህጉር እና አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ተነግሯል።
ለመጨረሻ ዙር የአሸናፊዎች አሸናፊ በውድድር ስነ ስርዓቱ ላይ የዋንጫ ሽልማትና ሰርተፍኬት የተዘጋጀ ሲሆን 1ኛ ለወጣ ለአሸናፊዎች አሸናፊ 50 ሺህ ብር የሚሸለም ሲሆን፤ 2ተኛ እና 3ተኛ ለወጡ አሸናፊዎች የ45 እና 40 ሺህ ብር ተሸላሚ ይሆናሉ ተብሏል።
ይህ ውድድር ላለፉት 10 አመታት የተካሄደ ሲሆን ተቋሙ በ2016 ዓም ሀገር አቀፍ የሒሳብ ትምህርት ውድድር፤ ከ50 ከተሞች በላይ የተውጣጡ ከ2 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች እና ከ3 መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎችን ማሳተፍ መቻሉ ተጠቁሟል።
ተቋሙ መጠሪያ ስያሜውን ያገኘው ከጃፓንኛ ቃል ሲሆን፤ ትርጓሜውም አባከስ ማለት መሆኑን የተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ አጥናፉ በዛሬው ዕለት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።



