#FastMereja I በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ ስማቸው ጎልቶ የሚነሳው የሁለት ዝነኛ ደራሲያን የጋራ ሥራ የሆነውና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿን የወይዘሮ ብርሃኔ አስፋውን የሕይወት ታሪክ የሰነደው “የጨረቃ ብርሃን” መጽሐፍ ዛሬ አርብ ታህሳስ 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል በድምቀት ተመረቀ።
መጽሐፉ “አዎ እዚህ ጋ ያመኛል” እና “በመኖር በኩል” በተሰኙ ተወዳጅ ሥራዎቹ በሚታወቀው ደራሲ አድኀኖም ምትኩ እና “ማሙሽ” የተሰኘውን መጽሐፍ ለንባብ ባበቃው ደራሲ ዮሐንስ አዝመራው በጋራ የተሰናዳ ነው።
ዛሬ በተካሄደው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የመጽሐፉ ባለቤት ወይዘሮ ብርሃኔ አስፋው፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የጥበብ ሰዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ታድመዋል።
“የጨረቃ ብርሃን” መጽሐፍ ትኩረቱን ያደረገው በ1954 ዓ.ም ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ በኋላ ሕይወታቸውን ለሴቶች መብት መከበርና ለጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መወገድ በሰጡት በወይዘሮ ብርሃኔ አስፋው ታሪክ ላይ ነው።
ወይዘሮ ብርሃኔ ራሳቸው በመሰረቱትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና ባለው “ኢንተር-አፍሪካን ኮሚቴ” አማካኝነት ለ27 ዓመታት በ28 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በተለይም የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ያደረጉት ተከታታይ ንቅናቄ በመጽሐፉ ውስጥ በዝርዝር ተሰንዷል። ለዚህ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ አበርክቷቸውም ለኖቤል የሰላም ሽልማት እጩ ሆነው መቅረባቸው ይታወሳል።
ወይዘሮ ብርሃኔ አስፋው በበኩላቸው ታሪካቸው በሁለቱ ብቁ ደራሲያን ተሰንዶ ለንባብ በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ መጽሐፉ ለወጣቱ ትውልድ በተለይም ለሴቶች ብርታትንና ተስፋን እንደሚሰጥ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
“የጨረቃ ብርሃን” መጽሐፍ ከዛሬ ጀምሮ በሁሉም መጻሕፍት መደብሮችና በአዟሪዎች እጅ ለገበያ መቅረቡም ታውቋል።




