#FastMereja I በአዲስ አበባ ከተማ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባውና እጅግ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችን ያሟላው “ሀባሪ ሜዲካል ፕላዛ” ዛሬ በደመቀ ሁኔታ ተመረቀ። ማዕከሉን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በጋራ መርቀውታል።
ሀባሪ ሜዲካል ፕላዛ ስድስት የመጥቶ ሂያጅ ሕክምና ማዕከላትና 15 የተለያዩ የሰብ-ስፔሻሊቲ ሕክምና አገልግሎቶችን የያዘ ሲሆን፣ በተለይም ኢትዮጵያውያን ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ውጭ አገራት በመሄድ የሚያወጡትን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላርና የሚገጥማቸውን እንግልት ለማስቀረት ታስቦ የተቋቋመ መሆኑ ተገልጿል።
የተቋሙ መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አከዛ ጠዐመ በምረቃው ወቅት እንደገለጹት፣ ማዕከሉ አዲስ አበባን የሕክምና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ካለው ራዕይ በመነሳት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ስልታዊ ትብብር ጀምሯል። በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ በኩል የሚያልፉ የትራንዚት መንገደኞች በቆይታቸው ወቅት የተሟላ የሕክምና ምርመራ አድርገው ውጤታቸውን በዲጂታል መንገድ የሚያገኙበት አሰራር መዘርጋቱን አስታውቀዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል በውጭ አገራት ብቻ ስናያቸው የነበሩ ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎቶች በሀገር ውስጥ እንዲገኙ ማስቻል ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው ተቋሙ መንግሥት ለቅድመ መከላከልና ለጥራት ሕክምና የሰጠውን የፖሊሲ አቅጣጫ በተግባር ለማገዝ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።
ማዕከሉ ከሕክምና አገልግሎቱ በተጨማሪ “HabariDoc” የተሰኘ መተግበሪያ በማበልጸግ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የዲጂታል ጤና አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ በአራት የአፍሪካ አገራትም አገልግሎቱን ለማስፋፋት ስምምነት ላይ ደርሷል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። በማዕከሉ የተመደቡ የሕክምና ባለሙያዎችም በጤና ሚኒስትሯ ፊት የሙያ መሐላ በመፈጸም ከዛሬ ጀምሮ በይፋ ሥራቸውን ጀምረዋል።




