banner

አራዳ ሞል ከአሜሪካው ታዋቂ ኩባንያ አሽሊ ፈርኒቸር ጋር ስምምነት ፈፀመ፡፡

#FastMereja I በአዲስ አበባ ከተማ፣ በፒያሳ ከአድዋ ሙዚየም ፊት ለፊት የተገነባው አራዳ ሌግዠሪ ሞል ከአሜሪካው ታዋቂ ፈርኒቸር አምራች አሽሊ ፈርኒቸር ጋር በትላንትናው እለት የስምምነት ፊርማ አከናውኗል፡፡ አሽሊ ፈርኒቸር የቤት ውስጥና የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶችንና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርብ አለም አቀፍ ኩባንያ ሲሆን በአለም ላይ ከአንድ ሺ በላይ ቅርንጫፎች ያሉት ነው፡፡

በ123 አገራት ውስጥ መደብሮች ያሉትና ከ35 ሺ በላይ ሰራተኞችን የሚያስተዳድረው ይህ ግዙፍ ኩባንያ ዋና መስሪያ ቤቱ በአሜሪካ ዊስኮንሲን ውስጥ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነውን ሾው ሩም በአራዳ ሌግዠሪ ሞል ውስጥ ለመክፈት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ስምምነቱን የፈፀሙት አራዳ ሞልና በአሽሊ ፈርኒቸር የኢትዮጵያ ተወካይ የሆነው ዩስራ ሆም ፈርኒቸር ናቸው፡፡ በስምምነት ስነስርአቱ ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር አርቪን ማሲንጋ ተገኝተዋል፡፡

አራዳ ሌግዠሪ ሞል በቀጣይነትም አለም አቀፍ ስም ያላቸውን ታዋቂ ብራንዶች በህንፃው ውስጥ ለማካተት ካለው እቅድ አኳያ ይህ ስምምነት በር ከፋች መሆኑን ባለቤቶቹ ገልፀዋል፡፡ በቅርቡ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የሚሆነው አራዳ ሌግዠሪ ሞል በተመሳሳይ ከሌሎች ታዋቂ አለም አቀፍና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት እንደሚያደርግም አስታውቋል፡፡

ጥቂት ስለአራዳ ሞል እንንገራችሁ፡፡
አራዳ ሌግዠሪ ሞል ከአድዋ ሙዚየም ፊት ለፊት የሚገኝ በ16,500 ካሬ ላይ ያረፈ ሲሆን ጠቅላላ የፍሎር ድምሩ 115,000 ካሬ ነው፡፡ ይህ ግዙፍ የሞል ፕሮጀክት ዲዛይንና ግንባታ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የህንፃ ምህንድስና ድርጅቶች የተሰራ ከመሆኑም በላይ በግንባታው ሂደት ላይ ከ1200 በላይ ሰዎች የስራ እድል አግኝተውበታል፡፡ ህንፃው በሚጠናቀቅበት ወቅት በሞሉ ውስጥ 48 ፐርሰንት የሚሆነውን ስፍራ የውጭ አገር ኩባንያዎች የሚይዙት ሲሆን የተቀረውን ደግሞ የተመረጡና በየዘርፉ የተሻለ ጥራት ያላቸው የአገር ውስጥ ድርጅቶችን ብቻ የማስገባት እቅድ የተያዘለት ነው፡፡ በሌግዠሪ ሞሉ ውስጥ በአገራችን ውስጥ ከተለመዱት አገልግሎቶች በተጨማሪ አለም አቀፍ ደረጃቸውን ያሟሉና በአይነታቸው አዲስ የሆኑ አገልግሎቶችን እንደሚያካትት የገለፀው አራዳ ሌግዠሪ ሞል እነዚህን አገልግሎቶች ምን እንደሚሆኑ ተጠይቆ ‹‹ወደፊት በሂደት እናሳውቃለን›› ብሏል፡፡





Leave a Comment