#FastMereja I የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በከተማዋ በሚካሄዱ የጎዳና ላይ ስብከቶች አማካኝነት የሚፈጠርን የድምፅ ብክለት ለመቆጣጠር ጥብቅ እርምጃ ሊወስድ እንደሆነ አስታውቋል።
የባለሥልጣኑ ሥራ አስኪያጅ ዲዳ ድሪባ ተቋሙ ክልከላ የሚያደርገው በስብከቱ ይዘት ሳይሆን በድምፅ መጠኑ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ድምጹ በሕግ ከተፈቀደው መጠን በላይ ሆኖ ከተገኘ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።
ይህ ውሳኔ የተላለፈው የጎዳና ላይ ስብከቶች ከፍ ባለ ድምጽ መሰማት በአካባቢው ነዋሪዎች እና ተገልጋዮች ላይ የሚፈጥረውን ረብሻ ለመከላከል መሆኑ ተነግሯል፡፡
“በአሁኑ ወቅት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው” ያሉት ስራ አስኪያጁ፡ በሚሰጠው ምክር እና ትምህርት የማይስተካከል ከሆነ ተቋሙ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ተናግረዋል።
ከድምፅ ብክለት ቁጥጥር በተጨማሪ፣ በጎዳና ላይ ስብከቱ ምክንያት የሚፈጠር አለመግባባት እና ግጭት በተደጋጋሚ እንደሚስተዋል ስራ አስኪያጁ አንስተው፤ መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ የሕግ አስከባሪ አካላት ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ከማናቸውም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚነሳ ድምጽ ብክለት እንዳያስከትል እና በአዋጅ ከተቀመጠው ልኬት በላይ እንዳይጨምር የመቆጣጠር ኃላፊነቱን መወጣቱ የከተማዋን ነዋሪዎች ጤናና ሰላም ለማረጋገጥ ሲባል የሚተገበር እንደሆነ አጽንኦት ተሰጥቶበታል።
ዘገባው የአሐዱ ሬዲዮ ነው።
