banner

ሳውዲ አረቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአልኮል ሽያጭ ፈቃድ ሰጠች

​#FastMereja I ሳውዲ አረቢያ ላለፉት 70 ዓመታት በሀገሪቱ ተግባራዊ አድርጋው የነበረውን ጥብቅ የአልኮል ክልከላ በማላላት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ አልኮል የሚሸጥበት ልዩ ሱቅ መክፈቷን አስታወቀች።

​ይህ ውሳኔ በሀገሪቱ ታሪክ ትልቅ ለውጥ ተደርጎ የተወሰደ ሲሆን፣ አተገባበሩ ግን በከፍተኛ ጥንቃቄ እና በተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ብቻ የተገደበ መሆኑ ተገልጿል።

​ሽያጩ የሚፈቀደው ሙስሊም ላልሆኑ የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች ብቻ ነው። ተጠቃሚዎች አስቀድመው በልዩ መተግበሪያ (App) መመዝገብና ከመንግስት ፈቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

​ሱቁ የተከፈተው በዋና ከተማዋ ሪያድ በሚገኘውና ኤምባሲዎች በሚገኙበት ዲፕሎማቲክ ኳርተር ውስጥ ነው።

የሳውዲ ዜጎች፣ ቱሪስቶች እና ሌሎች የውጭ ሀገር ነዋሪዎች ወደ ሱቁ መግባትም ሆነ መጠጥ መግዛት አይፈቀድላቸውም። በተጨማሪም ከ21 ዓመት በታች ለሆኑ ሰዎች ሽያጭ አይፈጸምም።

​እያንዳንዱ ዲፕሎማት በወር ውስጥ ሊገዛው የሚችለው የመጠጥ መጠን የተወሰነ ሲሆን፣ ለሌላ ሰው አሳልፎ መስጠትም በጥብቅ የተከለከለ ነው።

የሳውዲ መንግስት ይህን የወሰነው በዲፕሎማቲክ ቦርሳዎች አማካኝነት የሚደረገውን ህገ-ወጥ የአልኮል ዝውውር ለመቆጣጠር እና ሀገሪቱን ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች ምቹ ለማድረግ እንደሆነ ገልጿል።

​ይህ እርምጃ ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን ሀገሪቱን በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፍ ለማዘመን የቀረጹት “ቪዥን 2030” ስትራቴጂ አካል ተደርጎ ተወስዷል።

Leave a Comment