banner

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሚዲያ አካላት ጋር ተወያየ!

#Fastmereja:የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዛሬ በአዳማ ከተማ ከቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ጋዜጣ እና የማህበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ ኃላፊዎችና ኤዲተሮች ጋር የኮሚሽኑን ስራዎች እንዲሁም የመገናኛ ብዙሀን ተሳትፎ ዙሪያ ሰፊ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ ከመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት እና ከመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የተወከሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆን የሚዲያ ሚና ወሳኝ ቢሆንም፣ የሚሰሩ ዘገባዎች ግን ከወትሮው የተለየ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልጋቸዉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር አምባሳደር መሀሙድ ድሪር ገልፀዋል።

ሚዲያዎች አካታችነትን፣ ወካይነትን እና ግልጽነትን መርህ አድርገዉ እንዲሰሩም ጥሪ ቀርቧል።

በመድረኩ ላይ የኮሚሽኑ የዕቅድና ክትትል ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ጌታነህ ማሞ ባቀረቡት ሪፖርት፤ በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱን ለማስጀመር በትግራይና በአዲስ አበባ ከ20 ጊዜ በላይ ጥረት ተደርጎ ሳይሳካ መቅረቱን አስታውቀዋል።

ይህ መረጃ ኮሚሽኑ በክልሉ ያለውን ሂደት ለማስጀመር እያጋጠሙት ያሉ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ያመላከተ መሆኑን ነዉ የገለፁት።

ኮሚሽኑ ባለፉት አራት ዓመታት ያከናወናቸው ተግባራት ላይ ዝርዝር ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፣ በቀጣይ ስምንት ወራት ትኩረት የሚሰጣቸው አበይት ተግባራት ላይም ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር ምክክር ተደርጎባቸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ይህ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀጠና አልፎም ለዓለም ተምሳሌት የሚሆን ትልቅ ሥራ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጧል።

በዛሬዉ መርሀ-ግብር የውይይቱ ተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየታቸውን አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን ከኮሚሽኑ ጋር በቀጣይነት ስለሚያከናውኗቸው ተግባራትም ሀሳቦቻቸውን ገልፀዋል፡፡





Leave a Comment