banner

ለ10 ወራት በሰንሰለት ታስረው የቆዩት ሚስቶች ዘግናኝ የጭካኔ ታሪክ ይፋ ሆነ

​#FastMereja I በናይጄሪያ ካትሲና ግዛት የሚገኙ ሁለት ወጣት ሴቶች፣ ባለቤታቸው ለ10 ወራት ያህል በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ዘግቶ በሰንሰለት በማሰር የፈጸመባቸውን እጅግ አሰቃቂና ኢ-ሰብዓዊ ግፍ ለፍርድ ቤት ይፋ አደረጉ።

​ፋጢማ ሳሊሱ የ25 ዓመት ወጣት እና ሀዲዛ ሙሳ የ20 ዓመት ወጣት ሴቶች፣ ሳማኢላ ሙሳ በተባለው ባለቤታቸው የደረሰባቸውን ግፍ በመጥቀስ የጋብቻ ጥያቄያቸው እንዲፈርስ ለካትሲና ከፍተኛ የሸሪዓ ፍርድ ቤት አመልክተዋል። ግለሰቡ በፈጸመው በዚህ አሰቃቂ ድርጊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ በህግ እየታየ ይገኛል።

​ተጎጂዎቹ ለሚዲያ እንደገለጹት፣ ግለሰቡ ካገባቸው ጥቂት ቀናት በኋላ ነበር ወደ እስርና ድብደባ የገባው። ሀዲዛ ሙሳ እንደገለጸችው፣ ካገባት ከሁለት ሳምንት በኋላ እንቅስቃሴዋን በመገደብ በአንድ ክፍል ውስጥ በሰንሰለት አስሯታል። ፋጢማ በበኩሏ ካገባት ከአራት ቀናት በኋላ ድብደባ እንደጀመረባትና በኋላም ከሀዲዛ ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ በሰንሰለት ታስራ እንድትቆይ መደረጉን ተናግራለች።

​ሴቶቹ በቆዩባቸው 10 ወራት ውስጥ የደረሰባቸው ግፍ እጅግ ዘግናኝ ከመሆኑም በላይ ለሰሚ የሚከብድ ነው። እንደ ተጎጂዎቹ ምስክርነት ባለቤታቸው የፈጸመባቸው ድርጊቶች የራሳቸውን ፀጉርና ጥፍር በመላጨትና በመቁረጥ ከምግባቸው ጋር ቀላቅሎ እንዲበሉ ማስገደድ። በዓይናቸውና በብልታቸው ላይ ቃሪያ በርበሬ በመነስነስ ከፍተኛ ስቃይ እንዲደርስባቸው ማድረግ። ሁለቱንም ሴቶች በአንድ ክፍል ውስጥ አስሮ አንደኛዋ ባለችበት ሌላኛዋን ለወሲብ ማስገደድ። በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ታስረው እንዲበሉ፣ እንዲተኙና እዛው ክፍል ውስጥ እንዲጸዳዱ መገደዳቸው ይጠቀሳል።

​ሀዲዛ እንደገለጸችው፣ ግለሰቡን ያገኘችው በመንገድ ላይ ንግድ ስታከናውን ሲሆን፣ ቤተሰቦቿ መጀመሪያ ላይ ጋብቻውን ባይፈቅዱም ግለሰቡ “እንከባከባታለሁ” በሚል በገባው ቃል ተታለው ጋብቻው መፈጸሙን ተናግራለች። ፋጢማም በተመሳሳይ በጓደኛው አማካኝነት እንደተዋወቁትና በሳምንት ጊዜ ውስጥ ጋብቻው መፈጸሙን ገልጻለች።

​በአሁኑ ወቅት ተጎጂዎቹ በሰውነታቸው ላይ የሚታዩ በርካታ የድብደባ ጠባሳዎችን ለፍርድ ቤት ያሳዩ ሲሆን፣ ከዚህ “የሲኦል ኑሮ” ለመገላገል ፍቺ እንዲፈቀድላቸው እየተማጸኑ ይገኛሉ። የካትሲና ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ያዋለው በጥር ወር ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የክስ ሂደቱ ቀጥሏል።

Leave a Comment