📌 ኢራን ‘ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሬያለሁ’ ስትል ትራምፕ የባሕር ኃይል እንደሚያሰማሩ አስጠነቀቁ
#FastMereja I በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የዓለማችን ወሳኝ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር በሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ የሆርሙዝ ወሽመጥ በአሁኑ ወቅት በኢራን የባሕር ኃይል “ሙሉ ቁጥጥር” ስር መሆኑን አስታውቋል። የኢራን ባለሥልጣናት ማንኛውም መርከብ በወሽመጡ ማለፍ እንደማይችልና እስካሁን ከ10 በላይ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ኢላማ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው የነዳጅ መርከቦችን ታጅበው እንዲያልፉ ለማድረግ የአሜሪካ የባሕር ኃይልን “በተቻለ ፍጥነት” እንደሚያሰማሩ አስታውቀዋል። “አሜሪካ የኃይል አቅርቦት በነፃነት እንዲዘዋወር ታደርጋለች” ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ዝተዋል።
በውጥረቱ ምክንያት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በ13 በመቶ በመጨመር በአንድ በርሜል ከ82 ዶላር በላይ ሆኗል። ይህም ከሐምሌ 2024 ወዲህ ከፍተኛው ዋጋ ነው።
በአሁኑ ወቅት ወደ 3,200 የሚጠጉ መርከቦች በባህረ ሰላጤው ውስጥ ቆመው የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎች 500 መርከቦች ደግሞ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስና በኦማን ወደቦች አካባቢ ጥበቃ ላይ ናቸው።
ይህ የኢራን እና የአሜሪካ ፍጥጫ የዓለምን የንግድ እንቅስቃሴና የነዳጅ አቅርቦት በእጅጉ እያወከው ይገኛል።
