banner

ሴሬብራል ፓልሲ ላለባቸው ልጆች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተዘጋጀ!

#Fastmereja I አዲስ አበባ የአደይ ሴሬብራል ፓልሲ በጎ አድራጎት ማህበር(ACPO) በመጪው መጋቢት 13 ቀን 2018 ዓ.ም በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ሀገር አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የምስረታ መርሃ ግብር እንደሚያካሂድ አስታወቀ።

ማህበሩ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው፣ ዝግጅቱ“ሴሬብራል ፓልሲ ላለባቸው ልጆች ሁሉን አቀፍ የወደፊት ሁኔታ መገንባት” እና ”’በድርጊት ውስጥ ማካተት” በሚሉ መሪ ቃላት የሚመራ ይሆናል።

የመድረኩ ዋና ዓላማ በህብረተሰቡ ዘንድ ስለ ሴሬብራል ፓልሲ (Cerebral Palsy) ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ በመቅረፍ፣ ስለ መልሶ ማቋቋም (Rehabilitation) አገልግሎቶች አስፈላጊነት ግንዛቤ መፍጠር እና ለማህበራዊ ድጋፍ መጠናከር ጥሪ ማቅረብ እንደሆነተገልጿል።

በዕለቱ በሚካሄደው መርሃ ግብር ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ስለ ሴሬብራል ፓልሲ ሳይንሳዊ ግንዛቤ እና ስለ ህክምና አማራጮች ማብራሪያ የሚሰጡ ሲሆን፣ የህጻናቱ ወላጆች እና ተንከባካቢዎችም በዕለት ተዕለት ህይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች እና የሚሹትን ድጋፍ በተመለከተ የግል ተሞክሮአቸውን እንደሚያካፍሉ ተጠቁሟል።

በተጨማሪም የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የልማት አጋሮች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች በመድረኩ ላይ ተገኝተው ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ እና በትብብር ለመስራት ቃል የሚገቡበት መድረክ እንደሚሆንም ተመላክቷል።

ሴሬብራል ፓልሲ በልጅነት ጊዜ የሚከሰት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን፣ ሚዛንን እና አቀማመጥን የሚጎዳ የነርቭ ሁኔታ ሲሆን፤ ይህም የሚከሰተው አንጎል ገና በማደግ ላይ እያለ (ብዙውን ጊዜ ከመወለዱ በፊት ወይም በወሊድ ወቅት) በሚደርስ ጉዳት እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች፣ በቂ የኦክስጅን አቅርቦት ወደ አንጎል አለመድረስ እና ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የጭንቅላት ጉዳት ዋነኛ መንስኤዎች እንደሆኑ በመግለጫው ላይ ተመላክቷል።

በወይዘሮ ማስተዋል ሰማኸኝ በነሀሴ ወር 2016 ዓ.ም የተመሰረተው የአደይ ሴሬብራል ፓልሲ በጎ አድራጎት ማህበር(ACPO)፣ ሴሬብራል ፓልሲ ያለባቸው ህጻናት እና ቤተሰቦቻቸው በክብር እና በእኩልነት የሚኖሩበትን ማህበረሰብ ለመፍጠርዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡





Leave a Comment