#Fastmereja: ትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማኅበር ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕፃናትን ለመደገፍና በኅብረተሰቡ ውስጥ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ “በነሱ ጫማ” የተሰኘ ታላቅ የእግር ጉዞ መርሃ-ግብር በመጪው መጋቢት 20 ቀን 2018 ዓ.ም ሊያካሂድ መሆኑ ተገለፀ።
ማኅበሩ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በመጪው መጋቢት 20/2018ዓ.ም በሀይሌጋርመንት በሚካሄደው በዚህ የእግር ጉዞ መርሃ-ግብር ላይ ከ5,000 በላይ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዝግጅቱ ዋና ዓላማ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕፃናትና እናቶቻቸው በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚገጥሟቸውን ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ለኅብረተሰቡ ማስገንዘብ እንደሆነ ተገልጿል።
ከግንዛቤ ማስጨበጫው ባለፈ፣ መርሃ-ግብሩ ማኅበሩ እያስገነባው ለሚገኘውና ”የተሰጡ ልቦች” ተብሎ ለተሰየመው የ G+6 ሁለንተናዊ ድጋፍ መስጫ ማእከል ግንባታ የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ የታለመ ነው፡፡
ይህ ግንባታ የልጆች ማቆያና መመገቢያ የያዘ እና ባለ ስድስት ወለል ሲሆን በአንድ መቶ አርባስድት ሚሊዬን ብር በጀት ሊገነባ መሆኑንም የማህበሩ መስራች እና ስራ አስኪያጅ ሲስተር አሳየች ይርጋ ገልፀዋል።
ይህ ማእከል ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር፣ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ሕፃናት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በመስጠት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡
ይህ “በነሱ ጫማ” የተሰኘው የእግር ጉዞ፣ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ዜጎች በሰብአዊነትና በእኩልነት ለመደገፍ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
ትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማኅበር ላለፉት 19 ዓመታት በኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ተመዝግቦ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ሲንቀሳቀስ የቆየ አንጋፋ ድርጅት ነው፡፡
ማኅበሩ እስካሁንም ባደረገው እንቅስቃሴ ከ12 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ ልዩ ፍላጎት ባላቸው ሕፃናት ላይ አድርጎ እየሰራ መሆኑን አመልክቷል።




