banner

የምርጫ ቦርድ ማስጠንቀቂያ፦ “መመዝገብ መብት እንጂ ግዴታ አይደለም፤ ዜጎችን ማስገደድ ይቆም!”

#FastMereja I የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ምዝገባ ሂደት ላይ እየታዩ ያሉ የህግ ጥሰቶችን አስመልክቶ ጠንካራ መግለጫ አውጥቷል። ቦርዱ ዜጎች ለምርጫ ካልተመዘገቡ “ደመወዝ ይቆረጣል፣ ማህበራዊ አገልግሎት አታገኙም” በሚል የሚደረጉ ማስፈራሪያዎች ህገ-ወጥ መሆናቸውንና በአስቸኳይ እንዲቆሙ አዝዟል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን አጠቃላይ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ አስገዳጅና ህገ-ወጥ ድርጊቶች እየተፈጸሙ መሆኑን በሪፖርት እንደደረሰው አስታውቋል።

እንደ ቦርዱ መግለጫ ከሆነ፣ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት በየቤቱ በመዞር ዜጎችን ለምዝገባ ማስገደድ፣ ካልተመዘገቡ ደመወዝ እንደሚቀነስ ወይም ከስራ እንደሚሰናበቱ መዛት፣ እንዲሁም ከመሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶች ጋር በማያያዝ ጫና መፍጠር በግልጽ ታይቷል። ይህ ድርጊት የምርጫውን ነጻና ፍትሃዊነት የሚገታ በመሆኑ ቦርዱ የሚከተሉትን ነጥቦች አጽንኦት ሰጥቷል፦

📌 ማንኛውም ዜጋ የመምረጥ መብቱን ለመጠቀም መመዝገብ ያለበት በራሱ ፍላጎትና ውሳኔ ብቻ መሆን አለበት። መመዝገብ “ግዴታ” አይደለም።

📌 በምዝገባ ካርድ ሰበብ የዜጎችን ደመወዝ መቁረጥ ወይም አገልግሎት መከልከል ፍጹም ህገ-ወጥ ድርጊት በመሆኑ ቦርዱ በፅኑ ይቃወማል።

📌 ሁሉም የክልል መንግስታትና የከተማ አስተዳደሮች በስራቸው ያሉ አስፈጻሚዎች ከእንዲህ ዓይነቱ የቤት ለቤት ጫና እንዲታቀቡ ቦርዱ በደብዳቤ አሳስቧል።

📌 ይህንን ህገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ አካላትና ተቋማት ተለይተው ለህዝብ ይፋ እንደሚደረጉና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም በምርጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫ ሂደት እንዳይካሄድ እስከማገድ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ ቦርዱ አስጠንቅቋል።

በመጨረሻም ቦርዱ ዜጎች መብታቸውን ተገንዝበው ያለምንም ጫና በራሳቸው ፍላጎት እንዲመዘገቡ፣ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸውም ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Leave a Comment