#FastMereja I ጋዜጠኛ ዘወትር ደስአለኝ አርትስ ቲቪ ይዞት የመጣውን አዲሱን የዲጂታል መተግበሪያ “አርትስ ፕላስን” (Arts Plus) በይፋ መቀላቀሉ ታወቀ። ዛሬ በተሰጠው መግለጫ መሠረት፣ ዘወትር ደስአለኝ “Addis Pulse” የተሰኘና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ የሚያሳትፍ የእንግሊዘኛ ፖድካስት በማዘጋጀትና በማቅረብ ወደ ስራ ገብቷል።
የአርትስ ፕላስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ራፋቶኤል ወርቁ እንደገለጹት፣ አዲሱ የዲጂታል መተግበሪያ ፊልሞችን፣ ድራማዎችን፣ ሲትኮሞችንና ፖድካስቶችን በጥራት ለተመልካች የሚያቀርብ መድረክ ነው። ጋዜጠኛ ዘወትር ደስአለኝ በበኩሉ አርትስ ፕላስን መቀላቀሉ ህልሙን የሚያሳካበት ትክክለኛ ምርጫው መሆኑን ገልጾ፣ ኢትዮጵያውያንን የሚያኮራ ስራ ይዞ እንደሚመጣ ቃል ገብቷል።
በተያያዘ ዜና፣ አርትስ ፕላስ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና የቱሪዝም መዳረሻዎች ለዓለም የሚያስተዋውቅ “The Origin” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ሊያቀርብ መሆኑን አስታውቋል። ከዚህ ዝግጅት መካከል “The Origin – Oromia” የተሰኘውን ሁለተኛ ምዕራፍ ታዋቂዋ ቲክቶከር የአብስራ ፍፁም እንድታቀርብ (Host) በፊርማ ስነ-ስርዓት ተረጋግጧል።
ሌሎች ክልሎችን የሚዳስሱ ዘጋቢ ፊልሞች በማን እንደሚቀርቡ በቀጣይ ይፋ እንደሚደረግም በመግለጫው ተመልክቷል።
መጋቢት 25 ቀን 2018 ዓ.ም.




