#FastMereja I ቴምር ፕሮፐርቲስ ከአስረኛ ዓመት የምስረታ በዓሉ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የሼባማይል (ShebaMiles) የሽርክና ስምምነት ተፈራረመ። ስምምነቱ ደንበኞች ቤት ሲገዙ ለበረራ የሚያገለግሉ ማይሎችን በስጦታ እንዲያገኙ ያስችላል።
ቴምር ሪል ስቴት “በቤትዎ ዓለምን ይዘሩ” በሚል መሪ ቃል ዛሬ መጋቢት 29 ቀን 2018 ዓ.ም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ልዩ የአጋርነት ስምምነት ተፈራርሟል። ይህ ስምምነት በሪል ስቴት ዘርፍ አዲስ አሰራር ሲሆን፣ ደንበኞች በከፈሉት የገንዘብ መጠን ልክ የአየር መንገድ ማይሎችን እንዲያጠራቅሙ ዕድል ይሰጣል።
በስምምነቱ መሰረት ከ50% በታች ለከፈሉ ደንበኞች ለእያንዳንዱ 1 ዶላር 2.5 ማይል፤ 50% እና ከዚያ በላይ ለከፈሉ ደንበኞች ደግሞ ለእያንዳንዱ 1 ዶላር 3.5 ማይል በስጦታ ይሰጣል።
ተቋሙ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት በማሰብ በዶ/ር በላይ አበጋዝ የተመሰረተውንና በርካታ የልብ ህሙማን ህፃናት በውጭሀገራት እና በሀገር ውስጥ የልብ ህክምናን እንዲያገኙ በትጋት እየሰራ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከልን ለ18 አመታት ለመሩት ለዶ/ር ህሩይ አሊ የ300ሺ ማይልስ ስጦታ አበርክቷል፡፡
ኩባንያው በአስረኛ ዓመት ክብረ በዓሉ 58 ቤት ለገዙ ደንበኞች የዕጣ ማበረታቻ ያዘጋጀ ሲሆን፣ ዕድለኛ ለሆኑ ሁለት ደንበኞች እያንዳንዳቸው 4 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ዘመናዊ መኪኖችን በድምሩ በ8 ሚሊዮን ብር ወጪ አበርክቷል። በተጨማሪም ለአራት ደንበኞች የ1 ሚሊዮን ብር የቤት ውስጥ የማጠናቀቂያ ስራ በነፃ አከናውኗል።
የቴምር ፕሮፐርቲስ ጄነራል ማናጀር አቶ ጃፋር መሀመድ በዝግጅቱ ላይ ሲናገሩ “እኛ የምንገነባው ቤትን ብቻ ሳይሆን እምነትን ነው” ብለዋል። አያይዘውም እንደ አየር መንገድ ካሉ ግዙፍ ተቋማት ጋር መስራት የኩባንያውን ዓለም አቀፋዊ የአሰራር ዘይቤ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።




