banner

አንድ ግለሰብ ከ200 ሺህ ብር በላይ የሰረቀውን ሌባ በቁጥጥር ስር አዋለ

​#FastMereja I በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ ቆንዳ ከተማ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ሲሰራ የቆየ ሰራተኛ፣ ከ200 ሺህ ብር በላይ ሰርቆ ሲያመልጥ በአንድ ግለሰብ ብርታትና ክትትል እጅ ከፍንጅ ተያዘ። ግለሰቡ ሌባውን በቁጥጥር ስር ለማዋል እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረጉን ገልጿል።

​በገዋታ ወረዳ ቆንዳ ከተማ በሚገኘው “አቦል ሆቴል” ውስጥ በአስተናጋጅነት ሲሰራ የቆየ አንድ ወጣት፣ ትላንት ምሽት 201,780 (ሁለት መቶ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሰማንያ) ብር ሰርቆ መሰወሩ ታውቋል። የሆቴሉ ባለቤቶች ሰራተኛው መጥፋቱን ለፖሊስ ቢያመለክቱም፣ ገንዘብ መዘረፉን ያወቁት ግን ከረፋደ መሆኑ ተገልጿል።

​ወንደር አንዲሮ የተባለ ግለሰብ ከጊንቦ ወረዳ ወደ ቆንዳ ሲጓዝ፣ የተጠረጠረውን ወጣት መንገድ ላይ በእግር ሲጓዝ ይመለከተዋል። በሆቴሉ አስተናጋጅ እንደሆነ የሚያውቀው ግለሰቡ ሁኔታው አጠራጣሪ ሆኖ ስላገኘው ለሆቴሉ ባለቤቶች በስልክ ደውሎ መረጃ በመለዋወጥ፣ ግለሰቡ የጠፋው ሰራተኛ መሆኑን አረጋግጧል።

​እንደ መረጃው አቅራቢ ገለጻ፣ ተጠርጣሪው ለማምለጥ ቢሞክርም በሞተር ብስክሌት በመከታተልና እስከገባበት ቦታ ድረስ በመከተል፣ በፈጠረው እልህ አስጨራሽ ትግል በቁጥጥር ስር ሊያውለው ችሏል። ወዲያውኑ ለአካባቢው ሚሊሻ እና ለኮበች ከተማ ፖሊስ ጥሪ ተደርጎ፣ ግለሰቡ ከሰረቀው 201,780 ብር ጋር ለህግ አካላት ተረክቧል።

​ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ “ሌባን ማጋለጥ ውስጤ ነው” በማለት የተሰማውን ደስታ የገለጸ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ተጠርጣሪው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል።

​ሚያዝያ 2 ቀን 2018 ዓ.ም

Leave a Comment