#FastMereja I ሄይኒከን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈውንና የአጋቬ ጣዕም የተጨመረበትን “ዴስፔራዶስ” (Desperados) የተሰኘ ቢራ በዛሬው ዕለት ለኢትዮጵያ ገበያ ማስተዋወቁን በይፋ ገለጸ።
ሄይኒከን ኢትዮጵያ ሚያዝያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ይህ አዲስ ምርት በሀገሪቱ የፕሪሚየም ቢራ ዘርፍ ላይ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትና ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረው ነው ተብሏል። ከ50 በላይ በሚሆኑ ሀገራት የሚገኘውና ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የቆየ ታሪክ ያለው ዴስፔራዶስ፣ የቢራንና የጥሩ አልኮል መጠጦችን (Spirits) ጣዕም በማዋሃድ የተዘጋጀ ልዩ መጠጥ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ መጠጥ 5.9% የአልኮል መጠን ያለው ሲሆን፣ በተለይም አዳዲስ ነገሮችን ለሚፈልጉና ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን ለሚከተሉ ወጣቶች ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ ተነግሯል። ኩባንያው ምርቱን ለገበያ ያቀረበው የወጣቶችን የመዝናኛ ፍላጎትና ተለዋዋጭ የገበያ ሁኔታን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነም ጠቁሟል።
በተጨማሪም ሄይኒከን ኢትዮጵያ ምርቱን ለማስተዋወቅ ከአዳዲስ የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር “አቬኒዳ ዴስፔራዶስ” (Avenida Desperados) የተሰኙ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችን ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርብ አስታውቋል። ይህ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ብራንድ በሀገር ውስጥ መመረቱ ኩባንያው በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ያለውን የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነትና እምነት ዳግም የሚያረጋግጥ መሆኑን የኮርፖሬት ጉዳዮች ዳይሬክተር ንጉሥ አለሙ በመግለጫው አረጋግጠዋል።




