banner

ሐበሻ ቢራ የማምረት አቅሙን በ 5 እጥፍ አሳደገ!

#Fastmereja:የዛሬ 15 ዓመት “ኢትዮጵያዊ ማንነትን የሚገልጽ የቢራ ፋብሪካ ለምን አይኖረንም?” በሚል ጥያቄ የጀመረው የሀበሻ ቢራ ህልም፣ ዛሬ ለደረሰበት ግዙፍ ስኬት መሰረት የሆኑት መስራቾች ደማቅ የእውቅና እና የምስጋና መርሀ-ግብር በሸራተን አዲስ ሆቴል በደማቅ ስነ-ስርአት አከናዉኗል።

በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደዉ ልዩ የክብር ፕሮግራም ላይ፣ የኩባንያው ጠንሳሾች አቶ እስክንድር ደስታ እና ኢንጂነር መስፍን አቢ የላቀ ምስጋና ቀርቦላቸዋል፡፡

መስራቾቹ የዛሬ 15 ዓመት ጉዞውን ሲጀምሩ ዓላማቸው ፋብሪካ መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ “በእያንዳንዷ ጠርሙስ ላይ የኢትዮጵያን ኩራት ማተም” እንደነበር የተገለፀ ሲሆን በወቅቱ የነበረው ተግዳሮት ቀላል ባይሆንም፣ በተለይም ለቢራ ጠመቃ የሚሆን ንጹህ ውሃን በበቂ ሁኔታ ከማግኘት ጀምሮ ፋብሪካውን በሀገር በቀል ተቋራጮች ለማስገንባት የነበረው ውሳኔ የባለራዕዮቹን ጽናት የፈተነ እንደነበር ገልፀዋል።

በወቅቱ ተስፋንና ቴክኒካል ባለሙያዎችን ብቻ ይዞ ፋብሪካውን በእግሩ ማቆም ይቻላል ወይ?” የሚሉ ጥርጣሬዎች በነበሩበት ወቅት፣ መስራቾቹ ያሳዩት ብርታት ዛሬ 8,800 ኢትዮጵያውያን ባለአክሲዮኖች የሆኑበትን ግዙፍ ተቋም እውን ለማድረግ ማስቻሉ ተገልጿል።

ሀበሻ ቢራ ስራ ሲጀምር በዓመት 350,000 ሄክቶ ሊትርለማምረት አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የማምረት አቅሙን በማሳደግ በዓመት 1.5 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር እያመረተ ይገኛል።

ከዚህም በተጨማሪ ከአንድ የቢራ ምርት ተነስቶ አሁን ላይ አምስት የተለያዩ አማራጮችን ለገበያ ማቅረብ መቻሉ የኩባንያው የዕድገት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።

በእውቅና ፕሮግራሙ ላይ አቶ እስክንድር ደስታ እና ኢንጂነር መስፍን አቢ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የ”ሀበሻ ቢራ ቤተሰብ“ ከፍተኛ ምስጋና የቀረበ ሲሆን “የራሳችን” የሚለውን ኩራት በኢንዱስትሪው ውስጥ ስላቆሙና ለሀገር በቀል ባለሀብቶች ትልቅ አርአያ ስለሆኑ የላቀ ክብር እንደሚገባቸው ተገልጿል።

ይህ የ15 ዓመታት ጉዞ የጥቂት ግለሰቦች ስኬት ሳይሆን፣ የሺዎች ሰራተኞች ትጋትና የ8,800 ባለአክሲዮኖች የማይናወጥ እምነት ውጤት መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በቀጣይም ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለደንበኞቻቸው ማቅረባቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።





Leave a Comment