banner

የሃጫሉ ሁንዴሳ ወንድም “ዝምታዬ ይበቃል” ሲል ግልጽ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

​#FastMereja I ​የታዋቂው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ወንድም ሲሳይ ሁንዴሳ፣ ከአርቲስቱ ህልፈት በኋላ ለዓመታት ሲታዘባቸው የቆዩ ኩነቶችን አስመልክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላለፈ። ሲሳይ ይህን መልዕክት ያስተላለፈው “ዝምታን እንደ መስማማት ለሚቆጥሩ” አካላት ምላሽ መስጠት ግዴታ ሆኖ አግኝቼዋለሁ በማለት ነው።

​ሲሳይ ሁንዴሳ ባወጣው መግለጫ፣ ከአርቲስቱ ሞት በኋላ “ወዳጅ መሳይ ገዳዮች” እና “የቅርብ ነን የሚሉ ግለሰቦች” ሲፈጽሟቸው የነበሩ ድርጊቶችን “ፍጹም ነውር” ሲል ገልጿቸዋል። እስካሁን ዝምታን የመረጠው ከድርጊቶቹ ጀርባ ያለውን ድብቅ ፍላጎት ስለሚረዳ እንደነበር የገለጸው ሲሳይ፣ ከእንግዲህ ግን የሃጫሉን ክብር እና ማንነት በሚመጥን መልኩ ግልጽና የማያሻማ መልስ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አስምሮበታል።

​በተለይም ከሃጫሉ መታሰቢያ ሐውልት ጋር ተያይዞ የሚታዩ እንቅስቃሴዎችን “ድራማ” ሲል የጠራው ሲሳይ፣ ሐውልቱ ተገነባ ከተባለ ቆይቶ ዛሬ እንደ አዲስ ይፋ መደረጉ የዚሁ ድራማ አካል ነው ብሏል። “እንዲህ እንደዛሬው የድል ማግስት ጀግኖች ከመብዛታቸው በፊት የወንድነት ጥጉ ከማይደርሱበት ስፍራ አርቀህ መስቀልህ በጀን” ሲልም የነበሩ ሁኔታዎችን በምሬት አስታውሷል።

​ሲሳይ በመጨረሻም፣ ሃጫሉን በትክክል አውቆ የተረዳ ሰው የሚገባውን ሐውልት በልቡ አንጾ ስለ ፍትሕ ብቻ ቀን እንደሚቆጥር ገልጾ፣ “የጊዜ ጉዳይ ነው” ሲል መልዕክቱን አጠቃልሏል።

Leave a Comment