banner

ደንበኛዬን ቀማከኝ በማለት አጎቱን የገደለው ወጣት በ14 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

​#FastMereja I ​የአሸዋ ደንበኞቼን ቀማህኝ በሚል በተፈጠረ አለመግባባት አጎቱን በአካፋ መትቶ የገደለው ወጣት ጌታሁን ረታ፣ በአዳማ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ14 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ።

​በአዳማ ከተማ ዳቤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነውና በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ተከሳሽ ጌታሁን ረታ፣ ከአጎቱ ከአቶ ቱሉ በዳዳ ጋር በአሸዋ ጫኝና አውራጅነት ሥራ ላይ ተሰማርተው ይሠሩ እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል። ይሁን እንጂ የተከሳሹ ደንበኞች ወደ አጎቱ በመሄዳቸውና የሥራ መቀዛቀዝ በመፈጠሩ በሁለቱ መካከል ቂም መቋጠሩ ተገልጿል።

​መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም. ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ በሥራ ቦታ በተፈጠረ የቃላት ልውውጥ፣ ተከሳሹ “ደንበኞቼን ለምን ትወስዳለህ?” በሚል ንዴት ለአሸዋ መጫኛ የሚጠቀምበትን አካፋ በአጎቱ አንገት ላይ በማሳረፍ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶባቸዋል። ጉዳት የደረሰባቸው አቶ ቱሉ በአዳማ ሆስፒታል ለ20 ቀናት በሕክምና ቢረዱም፣ ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም. ሕይወታቸው አልፏል።

​የአዳማ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ታምራት ጌታሁን እንደገለጹት፣ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን አጣርቶ ለአቃቤ ሕግ ካስረከበ በኋላ በከባድ ሰው መግደል ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል። ፍርድ ቤቱ ሚያዝያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በዋለው ችሎት፣ ድርጊቱ ጭካኔ የተሞላበት መሆኑን በማረጋገጥና የቅጣት ማቅለያዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ተከሳሹን በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

Leave a Comment