banner

የመቄዶንያ ግዙፍ ሕንፃ ግንባታ ማጠናቀቂያ 11 ኮንቴነር የፊኒሺንግ ዕቃዎችና ማሽነሪዎች ገቢ ተደረጉ

#FastMereja I መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሻራውን ያሳረፈበትና ርብርብ ያደረገበት ግዙፉ የመቄዶንያ የአዕምሮ ሕሙማንና አረጋውያን መርጃ ማዕከል ሕንፃ ግንባታን ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችሉ የፊኒሺንግ ዕቃዎችና ማሽነሪዎች ገቢ መደረጋቸውን የማዕከሉ አመራሮች በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ከቻይናው ታዋቂ የኮንስትራክሽን ማሽነሪ አምራች ድርጅት “ኤክስ ኤም ጂ” (XMG) በቀጥታ የተገዙትና ጥራታቸውን የጠበቁ ባለ 40 ጫማ 11 ኮንቴነር ዕቃዎችና ማሽነሪዎች ማዕከሉ በደረሰበት ወቅትም የሚዲያ አካላት በተገኙበት አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የመቄዶንያ መሥራችና አመራሮች እንደገለጹት፤ አሁን ገቢ የሆኑት ዕቃዎችና ማሽነሪዎች ከ1 ዓመት በፊት የታዘዙ ሲሆን፣ ሕንፃውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ፣ ግንባታዎችን ለማከናወን፣ ግብዓቶችን ለማምረት እንዲሁም ለማጣራት የሚያገለግሉ ‘Full Set Concrete’ ማሽኖች ናቸው። ወደ ማዕከሉ ከገቡት ዋና ዋና ማሽነሪዎች መካከል የዊን ሎደር (Win loader)፣ የኮንክሪት ሚክሲንግ ፕላንት (Concrete mixing plant)፣ ታወር ክሬን (Tower crane)፣ የኮንክሪት ላይን ፓምፕ (Concrete line pump)፣ የኮንስትራክሽን ሊፍቶች (Construction lift)፣ የኮንክሪት ቡም ፓምፕ (Concrete boom pump)፣ የኮንክሪት ትራክ ሚክሰሮች (Concrete truck mixer)፣ ጄኔሬተሮችና ኤክስካቫተሮች ይገኙበታል። ከማሽነሪዎቹ በተጨማሪም ለግንባታው የሚሆን ብረትና ለሁሉም ማሽኖች የሚያስፈልጉ አስተማማኝ ዋስትና (Warranty) ያላቸው መለዋወጫ ዕቃዎች (Spare parts) አብረው ገቢ ሆነዋል።

የኤክስ ኤም ጂ (XMG) የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ቢሮ ሠራተኞች ተጠሪ የሆኑት አቶ ጥላሁን ዳኘ በበኩላቸው፤ ማሽነሪዎቹ በቀጥታ ከአምራች ድርጅቱ መገዛታቸው ታላቅ የዋጋ ቅናሽ እንዲገኝ ማድረጉን ገልጸዋል። ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የራሱ ወኪል ቢሮና ብቃት ያላቸው ቻይናውያንና ኢትዮጵያውያን መካኒኮች ያሉት በመሆኑ፣ ወደፊት በማሽኖቹ ላይ ምንም ዓይነት የቴክኒክ ችግር ቢፈጠር በቀላሉና በፍጥነት ማስተካከል የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አረጋግጠዋል።

ማዕከሉ በአጠቃላይ ከኤክስ ኤም ጂ (XMG) ማሽነሪ ድርጅት ባለ 40 ጫማ 24 ኮንቴነር ዕቃዎችን ለመግዛት ውል የፈጸመ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ዕቃዎችም ወደፊት በተከታታይ የሚገቡ ይሆናል። መቄዶንያ ከዚህ ቀደም 54 ኮንቴነር ፖርስሊን፣ 7 ኮንቴነር ግራናይት እና 6 ኮንቴነር የባኞ ቤት ዕቃዎችን ማስገባቱን ያስታወሰው የማዕከሉ መግለጫ፤ አሁንም ተጨማሪ የግንባታ ማጠናቀቂያ ቁሳቁሶች ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት በሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁሟል። “መቄዶንያ በትንሽ ወጪ ብዙ ይሠራል” ያሉት የማዕከሉ ኃላፊዎች፣ ይህ ስኬት ሊመዘገብ የቻለው ከመንግሥት፣ ከሕዝብና ከባለሙያዎች የሚደረገው ያልተቋረጠ እገዛና ድጋፍ በመኖሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለኤክስ ኤም ጂ ሠራተኞች፣ ለመካኒኮችና ድጋፉን ላላቋረጠው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተገልጋዮቻቸው ስም ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።




Leave a Comment