#Fastmereja I በሀገራችን የቤት ልማት፣ ግንባታ እና ሪል እስቴት ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎችን ትስስር ለማጠናከርና ሀገራዊ የታዳጊዎች ስፖርት ፕሮጀክትን ለመደገፍ ታስቦ የተዘጋጀው የመጀመሪያው «የኢትዮ ሪል እስቴት ካፕ» ስፖርታዊ ውድድር በዛሬዉ እለት በአዲስ ስፖርት ፓርክ በይፋ ተጀምሯል።
ስድስት ታዋቂ የሪል እስቴት ኩባንያዎች የሚሳተፉበትና በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው ይህ እግር ኳስ ውድድር፥ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ሳምንታት እንደሚቆይም ነዉ የተገለፀዉ።
የውድድሩ ዋና ዓላማ መንግስት 300 ታዳጊዎችን አፍርቶ ለዓለም እና ለአፍሪካ ዋንጫ ለማድረስ የያዘውን ሀገራዊ የፓይለት ፕሮጀክት በገንዘብና በሀሳብ መደገፍ ሲሆን፣ በዘርፉ ያሉ አልሚዎችም እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፣ አጋርነት እንዲፈጥሩና ጤናማ የንግድ ውድድር እንዲያደርጉ ማጠናከር መሆኑ ተገልጿል።
የአርኪ ኤቨንት መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ግርማ እንደገለጹት፤ ውድድሩ በሪል እስቴት ኢንዱስትሪ ውስጥ ለሚሰሩ አካላት ለአካል ብቃት ብቻ ሳይሆን ለስራ ቅንጅትና ለአንድነት ትልቅ ፋይዳ አንዳለዉ አስረድተዋል።
አቶ ዮሀንስ አክለዉም ውድድሩ የሚካሄድበት አዲስ ስፖርት ፓርክ የሀገራቸውን ስም ያስጠሩ ታላላቅ አትሌቶች መታሰቢያ ያረፈበት በመሆኑ ልዩ ተምሳሌትነት እንዳለውም ጠቁመዋል።
ታዋቂው የእግርኳስ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እንደገለፁት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በታዳጊዎች ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ባለው ስራ ላይ የሪል እስቴት አልሚዎች በዜግነት ግዴታ ተነሳስተው ወደ ስፖርቱ ድጋፍ ይዘው መምጣታቸው ትልቅ በር የከፈተ ተግባር ነው ብለዋል።
የቀድሞው የኢቢኤስ (EBS) ስፖርት ጋዜጠኛ ፍስሃ በበኩሉ፥ እግር ኳስ ሰላምና አንድነትን የማውረድ ታሪካዊ አቅም እንዳለው ጠቅሶ፣ ተሳታፊ ኩባንያዎች በሜዳ ላይ ጤናማ ፉክክር እያደረጉ የስራ ውጥረታቸውን እንዲቀንሱና በጨዋታ ወቅትም ከፍተኛ ስሜታዊነትን በመቆጣጠር ሙያዊ ጨዋነታቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧል።
የሪል እስቴት ዘርፍ በሀገሪቱ የኢኮኖሚና የከተማ ውበት ግንባታ ላይ እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ ባሻገር፣ ይህ ውድድር አልሚዎቹ የሀገሪቱን የስፖርት ባህልና ማህበረሰባዊ ትስስር በጋራ ለመገንባት ቃል የሚገቡበት መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል።




