#FastMereja I በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረጃርሶ ወረዳ፣ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ይጓዙ በነበሩ ሁለት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ላይ ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት ቢያንስ ከስምንት በላይ ሰዎች መገደላቸውንና በርካቶች መታገታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጹ። ጥቃቱ የደረሰው ዛሬ ግንቦት 20 ቀን 2018 ዓ.ም ረፋድ 4 ሰዓት ገደማ፣ በጎሃፅዮን እና ገብረ ጉራቻ መካከል “ወሌ” በተባለ ልዩ ቦታ ላይ ነው።
የአካባቢው ነዋሪዎች ለቲክቫህ እንደገለጹት፣ ታጣቂዎቹ በአውቶቡሶቹ ላይ በከፈቱት ተኩስ የሰዎች ሕይወት ወዲያውኑ ያለፈ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር ከ8 እስከ 10 እንደሚደርስና ቢያንስ 10 ያህል ሰዎች ደግሞ ቆስለው ወደ ጤና ጣቢያ ተወስደዋል። ከተሳፋሪዎቹ መካከልም በርካቶቹ ታግተው ወደ አልታወቀ ቦታ ተወስደዋል። ጥቃቱን ተከትሎም መንገዱ ለተወሰነ ጊዜ ተዘግቶ እንደነበርና ተሽከርካሪዎች በጎሃፅዮን ከተማ ለመቆም መገደዳቸው ታውቋል።
ስለደረሰው ጥቃትና ስለተወሰደው እርምጃ ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ አካባቢው አመራሮች የተደረገው የስልክ ጥሪ ያልተመለሰ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጀይላን አብዲ በበኩላቸው ጥያቄዎች በጽሑፍ እንዲላኩላቸው ቢጠይቁም፣ ዘገባው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አለመስጠታቸውን ቲክቫህ አስታውቋል።
ይህ ጥቃት ከመፈጸሙ ከሳምንት በፊት፣ በተመሳሳይ ሁኔታ “አሊደሮ” በተባለ ስፍራ ከ60 በላይ ተሳፋሪዎችን የያዘ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ታግቶ እንደነበርና በዚህ ወር መጀመሪያ ላይም በዚሁ ወረዳ በ”ሸኔ” ታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ ከ8 በላይ ሰዎች መገደላቸውና ቤቶች መቃጠላቸው ይታወሳል።
