#FastMereja I ሲናፕስ ኢትዮጵያ (Synapse Ethiopia) የሀገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ለማዘመን ያለመ “የ2026 አገር አቀፍ የኒውሮፋይናንስ ጉባኤ” (National NeuroFinance Summit Ethiopia 2026) ሰኔ 9 ቀን በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ አስታወቀ።
ይህ ታሪካዊ ጉባኤ በባንክ፣ በኢንሹራንስ፣ በካፒታል ገበያ እና በመንግስት አካላት ላይ የሚገኙ ከፍተኛ የሥራ መሪዎችንና ውሳኔ ሰጪዎችን በአንድ መድረክ ያገናኛል።
በዚህም የውሳኔ አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል፣ የስጋት አስተዳደርን (risk management) ለማጠናከር እና የባህሪ ሳይንስን፣ የአዕምሮ ሳይንስን (Neuroscience) እንዲሁም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን (AI) ከፋይናንስ ጋር የሚያገናኘውን “ኒውሮፋይናንስ” እውቀት በሀገሪቱ ማስተዋወቅ ያለመም ነው።
መድረኩን በኒውሮሳይንስ እና በAI ዘርፍ ዓለም አቀፍና አገር በቀል ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ይመሩታል ተብሏል።
የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች የኒውሮፋይናንስን ምንነትና ፋይዳ ተረድተው በስራዎቻቸው ላይ እንዲተገብሩትም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ጥሪ ቀርቧል።
በጉባኤውም የሚጠበቁ ጉዳዮችንም ;- የብሔራዊ ኒውሮፋይናንስ አስፈጻሚ ግንዛቤ ሪፖርት (NeuroFinance Executive Insights Report) ይዘጋጃል።
በዲጂታል እምነት፣ በባህሪ ተኮር ስጋት አስተዳደር እና በፋይናንስ ፈጠራ ላይ የፖሊሲና የኢንዱስትሪ ምክረ ሃሳቦች ይቀርባሉ።
በባንኮች፣ ኢንሹራንሶች፣ ተቆጣጣሪ አካላት እና ባለሀብቶች መካከል ጠንካራ የመሪዎች ትስስር ይፈጠራል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኒውሮፋይናንስ ማህበረሰብ (National NeuroFinance Community) ይመሰረታል።
ሲናፕስ ኢትዮጵያ በኒውሮሳይንስ፣ በባህሪ ሳይንስ፣ በስትራቴጂክ አማካሪነት እና በመሪነት ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ድርጅት ሲሆን፣ ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ለመክፈት የተዘጋጀ ነው።




