banner

የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ሊጀመር ነው፡ ኮሚሽኑ የ4 ሺህ ተወካዮችን ዝግጅት አጠናቀቀ

#FastMereja I የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለቀጣዮች አራት ሳምንታት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። በጉባዔው ላይ ከወረዳ፣ ከክልል፣ ከፌዴራልና ከስደት ዓለም የተወጣጡ 4,000 ተወካዮች የሚሳተፉ ሲሆን፣ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የመስተንግዶ፣ የትራንስፖርትና የጸጥታ ቅድመ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን ኮሚሽኑ አረጋግጧል።

ይህ ግዙፍና ታሪካዊ ጉባዔ በዋናነት በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል የሚካሄድ ሲሆን፣ ማዕከሉ ለተሳታፊዎች ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ተደርጎ ተዘጋጅቷል። በተለይም እናቶችና ሴት ተሳታፊዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሕፃናት ማቆያ ስፍራዎች በባለሙያ የተደራጁ ሲሆን፣ ለአካል ጉዳተኞችና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖችም ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል። ተሳታፊዎች ቆይታቸውን በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ እና በፌደራል ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ግቢዎች ውስጥ እንደሚያደርጉ የተገለጸ ሲሆን፣ ባህልንና ማህበራዊ ደረጃን ያገናዘበ የምግብ፣ የንጽህናና የሕክምና አገልግሎት በጊዜያዊ ክሊኒኮች ጭምር እንደሚቀርብ ተገልጿል።

የትራንስፖርትና የጸጥታ ጉዳይን በተመለከተም ኮሚሽኑ ከፌደራልና ከክልል የጸጥታ አካላት እንዲሁም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር የተቀናጀ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል። ተሳታፊዎች ከየአካባቢያቸው ወደ አዲስ አበባ የሚገቡበት የአየርና የየብስ አማራጮች የተመቻቹ ሲሆን፣ በከተማው ውስጥም የትራንስፖርትና የቋንቋ እገዛ የሚያደርጉ በጎ ፈቃደኞች ተሰማርተዋል።

ኮሚሽኑ ተሳታፊዎች እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ አዲስ አበባ በመግባት ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ በአንዳንድ የግልና የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያሉ ተወካዮች የፈቃድ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ጠቁሟል።

በማቋቋሚያ አዋጁ ቁጥር 1265/2014 አንቀጽ 41 መሠረት ማንኛውም ተቋም ለኮሚሽኑ ሥራ ትብብር የማድረግ ግዴታ እንዳለበት በማሳሰብ፣ ተሳታፊዎች ያለምንም እንግልት በጉባዔው ላይ እንዲገኙ አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግላቸው በጥብቅ አሳስቧል። ኮሚሽኑ እስካሁን ከ1300 በላይ ወረዳዎችን በማሻገር ከመቶ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያካተቱ በርካታ አጀንዳዎችን መሰብሰቡን ገልጾ፣ ጉባዔው ስኬታማ እንዲሆን መላው ሕዝብ በጸሎትና በንቃት እንዲከታተል ጠይቋል።

Leave a Comment