banner

የሕፃናትን ምናብ ለማሳደግ የተዘጋጀው አዲስ የሕፃናት ትያትር ለታዳሚ ሊበቃ ነው!

#Fastmereja:-የሕፃናትንና የወጣቶችን አእምሮአዊ፣ ሥነ-ልቦናዊና ማኅበራዊ ዕድገት የሚያግዙ በርካታ ትምህርታዊና አዝናኝ ሥራዎችን ሲያቀርብ የቆየው የሕፃናትና ወጣቶች ትያትር ቤት፤ “የንባብ ከተማ” (በሌላ መጠሪያው “የፊደል ከተማ”) የተሰኘ አዲስና ድንቅ የሕፃናት ትያትር ዝግጅቱን አጠናቆ ለምረቃ ማብቃቱን አስታወቀ።

የሕፃናትን ረቂቅ ምናብ (Imagination) እና የፈጠራ ክህሎት ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀው ይህ ትያትር፤ በዓለም አቀፍ የትያትር አዘገጃጀት ስልት በፋንታሲ (Fantasy) ዘውግ የተቃኘ ሲሆን በትያትሩ ውስጥ ሕፃናትን ይበልጥ ለመሳብና ታሪኩን በቀላሉ እንዲረዱት ለማድረግ ሲባል፣ እንስሳትና ድንጋዮች ሕይወት አግኝተው እንዲናገሩና እንዲተገብሩ ተደርጎ በልዩ ጥበብ ተቀርጿል።

የትያትሩ ዋና አብይ ጭብጥ በትውልዱ ዘንድ የጠፋውንና እጅግ የሚፈለገውን የንባብ ባህል ማሳደግ ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ጎን ለጎን የሚሄደው ንዑስ ጭብጡ ደግሞ ሰላም፣ አንድነት፣ መዋደድና ፍቅርን ለሕፃናቱ በአንደበታቸውና በምስል በሚገባቸው መልኩ የሚያስተምር ስለመሆኑም ነዉ የተገለፀዉ።

የሕፃናት ትያትር እንደ አዋቂዎች ትያትር ሳይሆን ከፍተኛ ድካምና ጥንቃቄ የሚጠይቅ መሆኑን የገለጹት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ፤ ተዋንያኑ መድረክ ላይ ከሚገኙት ሕፃናት ጋር ቀጥተኛ፣ ሕያውና ንቁ ተሳትፎ (Active participation) እንዲያደርጉ የሚያስገድድ በመሆኑ ሥራውን ፈታኝና ማራኪ ያደርገዋል ብለዋል።

ይህንን ፈታኝ ጥበብ በብቃት ለመወጣትም ከተቋሙ የተገኙ 5 ወጣቶችና አንጋፋ ተዋንያንን ጨምሮ፣ ከተለያዩ ታዋቂ የጥበብ ተቋማት (ከማዘጋጃ ቤት ባህል አዳራሽ እና ከሀገር ፍቅር ትያትር) የመጡት እንደ ሚሊዮን ብርሃኔ እና ዮዲት አሰፋ ያሉ 2 አንጋፋ ባለሙያዎች በአጠቃላይ 8 ተዋንያን በትያትሩ ላይ ተሳትፈዋል። ትያትሩ ጥራት ባላቸው ዘመናዊ መብራቶችና ማራኪ ሙዚቃዎች የታጀበ በመሆኑ ለሕፃናቱ እጅግ ማራኪና ቀልብ ሳቢ ሆኖ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

ይህ ቀደም ሲል በአራት ኪሎ በነበረው ጠባብ አዳራሽ ውስጥ ለሕፃናት ድራማ የማይመች፣ የመጫወቻ ቦታ የሌለውና ወንበሮቹ ሕፃናትን ለውድቀት የሚዳርጉ እንደነበሩ አስታውሶ፤ አሁን ግን ይህ ችግር ተቀርፎ ሕፃናት በነፃነት የሚጫወቱበትና ቢወድቁ እንኳ በምቾት ምክንያት እንቅልፍ አሸንፏቸው እንጂ በጉዳት ስጋት እንዳይሆን ተደርጎ የተሠራ አዲስ አዳራሽ ማግኘታቸውን ገልጿል።

ይህ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው “የንባብ ከተማ” ትያትር ከሚቀጥለው እሁድ ጀምሮ በይፋ የሚከፈት ሲሆን፣ ዘወትር እሁድ ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ለታዳሚዎች የሚቀርብ ሲሆን ከተለመደው ትያትር በተጨማሪ ሙዚቃ፣ ተረት እና ሕፃናትን የሚያዝናኑና የሚያስተምሩ የታሪክመርሐግብሮች በፓኬጅ መልክ መካተታቸው ታውቋል።

ትያትሩ ተማሪዎችና ሕፃናት ለክረምት ዕረፍት በሚወጡበት በዚህ ወቅት መዘጋጀቱ ለወላጆችና ለልጆች ትልቅ መልካም አጋጣሚ መሆኑ ተገልጿል።

እንዲሁም ወላጆች ያለምንም ስጋት ልጆቻቸውን ይዘው በመምጣት እንዲያዝናኑ፣ የንባብ ባህላቸውን እንዲያሳድጉና ልጆቻቸውን በዚህ አዲስ ተቋም በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች በማሰልጠን ለነገ ትላልቅ ባለሙያዎች የሚሆኑበትን መሠረት እንዲጥሉ ጥሪ ቀርቧል።

#ኪነ_ጥበብ





Leave a Comment