banner

ፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ዉስንነት ብሄራዊ ማህበር የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ-ግብር አከናወነ!

#Fastmereja I «ፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ብሔራዊ ማህበር» በየዓመቱ የሚያዘጋጀውንና የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ህጻናትና ወጣቶች ልዩ ተሰጥኦ የሚታይበትን 18ኛውን ዓመታዊ የ«እኛም እንችላለን» በዓል እና የትምህርት መዝጊያ ፕሮግራም በዛሬዉ እለት በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ በደመቀ ሁኔታ አከበረ።

ዘንድሮ «እኛም የማህበረሰባችን አካል ነን (We are part of our community)» በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዚህ መርሃ ግብር ላይ ማህበሩ የሚያቀፋቸው ህጻናትና ወጣቶች ዘላጆች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ ልዩ ልዩ የዳንስ፣ የንግግር እና የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ክህሎቶቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ የአእምሮ እድገት ውስንነት ቢኖርባቸውም እንደማንኛውም ሰው የራሳቸው የሆነ የተለየ ችሎታና ታላንት እንዳላቸው በተግባር አሳይተዋል።

በዕለቱ በዓሉን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ የሸዋጌጥ ክብረት፣ ይህ መርሃ ግብር ልጆቹ ያላቸውን አቅም ለህብረተሰቡ የሚያሳዩበት ብቻ ሳይሆን፣ ባለፉት ዓመታት ማህበሩ በህብረተሰቡ ግንዛቤ ላይ ያመጣውን ትልቅ ለውጥ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ችግሩ ከእርግማንና ከኃጢአት ጋር ተያይዞ በስህተት ይታይ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን ሳይንሳዊ ግንዛቤው እያደገ መምጣቱንና መንግስትም በትምህርት ፖሊሲና በልዩ ፍላጎት ስትራቴጂዎች ውስጥ ጉዳዩን ማካተቱ ትልቅ እመርታ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ይህንን በዓል በደመቀ ሁኔታ ያከበረው «ፍቅርኢትዮጵያ» ማህበር፣ በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ16 ሺህ በላይ አባላትን ቢያቅፍም በከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ውስጥ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በአገሪቱ ከአራት ሚሊዮን በላይ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች አሉ ተብሎ ቢገመትም ማህበሩ መድረስ የቻለው ለጥቂቶቹ ብቻ በመሆኑ፣ በ22 አካባቢ በሚገኘው ማዕከሉ ለልጆቹ የሚሰጠውን የዳንስ፣ የስፖርትና የሙያ ስልጠና አጠናክሮ ለመቀጠል ህብረተሰቡ፣ በጎ ፈቃደኞችና ተቋማት በገንዘብ፣ በዕውቀትና በጉልበት የበኩላቸውን አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ማህበሩ ጥሪውን በድጋሚ አስተላልፏል።

#ማህበራዊ





Leave a Comment