banner

በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የሴቶች የሰላም ፎረም ተካሄደ!

#Fastmereja:-በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ እኩልነት እና ልማትን ለማምጣት የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ፣ አመራርእና የሰላም ትምህርት ወሳኝ መሆናቸው ተገለጸ።

ይህ የተባለው በአዲስ አበባ ኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል በተካሄደውና በርካታ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈው “የኢትዮጵያ ሴት መሪዎች የሰላም ፎረም” (Ethiopian Women’s Leaders Peace Forum) ላይ ነዉ።

በሴቶች ዓለም አቀፍ የሰላም ቡድን (IWPG) እና በኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ትብብር የተዘጋጀው ይህ ፎረም፣ “የሰላም ትምህርትን ማሳደግ፣ የሴቶች አመራር እና ዓለም አቀፍ አጋርነት” በሚል መሪ ቃል በይፋ ተከፍቷል።

የIWPG የልዑካን ቡድን በቅርቡ በቡሩንዲ፣ በታንዛኒያ እና አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ያደረገውን ጉዞ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን፣ በጉዟቸው ያገኟቸው ማህበረሰቦች ሁሉ ዋነኛ ፍላጎት “ዘላቂ ሰላም” መሆኑን ገልጸዋል።

በፎረሙ ላይ የተገኙት የHWPL የኢትዮጵያ ቀጠና ስራ አስኪያጅ ፖል በበኩላቸው፣ ድርጅታቸው ከIWPG እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN ECOSOC) ጋር በመሆን በኢትዮጵያና በአፍሪካ ህብረት ውስጥ በሰላም ዙሪያ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሴቶች ፌዴሬሽን አመራር፣ የሴቶች ማህበር ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ የተዘረጋ ጠንካራ መዋቅር ያለው፣ ከ54 በላይ አባል ማህበራትን ያቀፈና ከ8.6 ሚሊዮን በላይ ሴቶችን የሚወክል ግዙፍ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን መዋቅር በመጠቀምም ሴቶች በሀገሪቱ የሰላም ግንባታ እና ልማት ውስጥ ያላቸውን ቁልፍ ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ሰላም በድንገት የሚመጣ ሳይሆን በእያንዳንዱ ሰው ጥቃቅን ጥረቶች የሚገነባ መሆኑን ተጠቅሶ፤ ሴቶች የሰላም ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ሰላምን የሚፈጥሩ መሪዎች መሆናቸውን እና በአንድ ሴት ላይ የሚመጣ በጎ ለውጥ ቤተሰብን፣ ማህበረሰብን አልፎም ቀጣዩን ትውልድ እንደሚቀይር አስረድተዋል።

በፎረሙ ላይ የቀረበው ሌላው ቁልፍ መልዕክት ዘላቂ ሰላም በአንድ ተቋም ወይም ግለሰብ ጥረት ብቻ ሊረጋገጥ እንደማይችል ነው። ይልቁንም ከመንግስት፣ ከትምህርት ተቋማት (አካዳሚ)፣ ከሲቪል ማህበረሰብ፣ ከሴቶች፣ ከወጣቶች እና ከሚዲያ ጋር በጋራ በመተባበር እንዲሁም በ”ሰላም ትምህርት” አማካኝነት እንደሚገነባ አጽንኦት ተሰጥቶበታል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ተወካይ ለዓለም አቀፍ የሴቶች የሰላም ቡድን (IWPG) ስላደረገው ድጋፍና አጋርነት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣ ከቡድኑ ጋር የተጀመረው ትብብር ልምድ ለመለዋወጥ እና በቀጣይ በጋራ ለመስራት (በመግባቢያ ሰነድ ወይም Moሀ ጭምር በመደገፍ) ትልቅ በር የሚከፍት መሆኑን ጠቁመዋል።





Leave a Comment