banner

2ኛው የአዲስ አበባ ሆስፒታሊቲ እና ቱሪዝም እውቅናና ሽልማት ሊካሄድ ነው!

#Fastmereja:-የአዲስ አበባ ሆቴል እና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበር (AAHTPA) የ2ኛውን የከተማዋን የሆስፒታሊቲ እና ቱሪዝም እውቅናና ሽልማት መርሃ-ግብር የፊታችን ነሐሴ 23 ቀን 2018 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል እና ስፓ እንደሚያካሂድ በዛሬዉ እለት በተሰጠ መግለጫ ተገልጿል።

ማኅበሩ ይፋ ባደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ይህ የእውቅና መርሃ-ግብር ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሦስት ዓመታት በዘርፉ የታዩ አበይት አፈጻጸሞችን ለማበረታታት፣ የአገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ እና የላቀ ሙያዊ ብቃትን ለማጠናከርአልሞ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

በእውቅና መርሃ-ግብሩ ላይ በመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአካዳሚክ ተመራማሪዎች፣ የዘርፉ ባለሃብቶችና ባለሙያዎች በተገኙበት በ4 ዋና ዋና ዘርፎች ከ25 በላይ ሽልማቶች እንደሚሰጡ ተገልጿል።

ሽልማቶቹም የግል ሙያዊ ብቃትን፣ የድርጅቶችንና የሆቴሎችን አርአያነት፣ የማኅበረሰብና የአካባቢ ጥበቃ ተጽዕኖን እንዲሁም ለዘርፉ ዕድገት የሕይወት ዘመን አስተዋፅኦ ያበረከቱ አካላትን የሚዘክሩ ናቸው።

የአዲስ አበባ ሆቴል እና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህNC (AAHTPA) ፕሬዝዳንት አቶ አሸናፊ ሙሉጌታ እንደገለፁት የምርጫ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ በገለልተኝነትና በግልጽነት የተከናወነ ሲሆን፤ የአገልግሎት ጥራት፣ የደንበኞች እርካታ፣ የሥራ አካባቢ ምችት፣ የሙያ ሥነ-ምግባርና ሀገራዊ አስተዋፅኦ በዋና መመዘኛነት መያዛቸዉም ነዉ የተገለፀዉ።

ከእውቅና አሰጣጡ በተጨማሪ «የሆስፒታሊቲ ዘርፍ ለታላላቅ ኩነቶች፦ የኢትዮጵያን ቱሪዝም መፃኢ ዕድል መቅረጽ» በሚል ርዕስ ከፍተኛ የፓናል ውይይት የሚካሄድ ሲሆን ውይይቱ ሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችንና ታላላቅ ኩነቶችን (Mega-Events) በብቃት ለማስተናገድ የሚያስችላትን የተቀናጀ አሠራር በመንግሥት ፖሊሲ፣ በትምህርት ተቋማትና በሆቴሎች መካከል ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ሆቴል እና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበር ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የባለሙያዎችን አቅም በመገንባት፣ የሥራ ዕድል ትስስር በመፍጠር፣ የአሠሪና ሠራተኛ ውዝግቦችን በመፍታትና የሀገርን የበጎ ገጽታ በማስተዋወቅ ረገድ በርካታ አዎንታዊ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱ ይታወሳል።





Leave a Comment