banner

የዳግማዊ አጼ ምኒልክ፣ የእቴጌ ጣይቱ እና የፊታውራሪ ገበየሁ የልደት መታሰቢያ በዓል በድምቀት ተከበረ

​#FastMereja I በደብረ ብርሃን ከተማ ጠባሴ ክፍለ ከተማ በሚገኘውና የአጼ ምኒልክ የትውልድ ስፍራ በሆነው ታሪካዊው አንጎለላ “እንቁላል ኮሶ” ቀበሌ የዳግማዊ አጼ ምኒልክ 182ኛ፣ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል 186ኛ እና የፊታውራሪ ገበየሁ 182ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ በዓል ነሐሴ 12 ቀን 2018 ዓ.ም በድምቀት ተከብሮ ውሏል።

​በዚሁ የመታሰቢያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ አባት አርበኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ንጉሠ ነገሥቱ ሀገር ከመገንባትና የሀገርን ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ ከተጫወቱት ታሪካዊ ሚና ባሻገር እንደ መኪና፣ ስልክ፣ ኤሌክትሪክ፣ ባቡር፣ ባንክና ዘመናዊ ትምህርት ያሉ የዘመናዊነት መሰረቶችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለኢትዮጵያ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ተወስቷል። ከሁሉም በላይ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ አስተባብረው በታላቁ የአድዋ ድል ያቀናጁት ታሪካዊ ክስተት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ህዝቦች የነፃነትና የኩራት ተምሳሌት መሆኑ ተገልጻል።

​በተመሳሳይ በዕለቱ የአድዋው ጀግና የፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራው ታሪካዊ አስተዋጽኦ የተወሳ ሲሆን፣ ትውልዳቸው በአንጎለላ እስታቆላ ጎጥ የሆነው የዚሁ አርበኛ አጽም ከዓመታት በኋላ ወደ ትውልድ ስፍራቸው መጥቶ በአንጎለላ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ማረፉ ተነግሯል። በምክርና በጥበባቸው ለዛሬ ሴቶች አርአያ የሆኑት የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ታሪክም በስነ-ስርዓቱ ላይ በሰፊው ተዳሷል።

​በሌላ በኩል የአጼ ምኒልክ እትብት በተቀበረበት ስፍራ ላይ መታሰቢያ እንዲሆን በስማቸው የተሰየመው ጤና ጣቢያ አጥር የሌለውና በደረጃው መሟላት የሚገባቸው አስፈላጊ አገልግሎቶች ያልተሟሉለት በመሆኑ አሳዛኝ መሆኑ ተጠቅሷል። በመሆኑም ይህን ታሪካዊ ስፍራ የሚመጥን ደረጃ እንዲኖረው፣ የጎብኚዎች መረጃ ማዕከል እንዲቋቋምለትና መሰረተ ልማቱ ተሻሽሎ ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት ተረባርበው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ተላልፏል።

ባለሀገሩ አስጎብኚ ድርጅት፣ ከደብረብርሃን ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን መርሃ ግብሩን አዘጋጅተውታል።





Leave a Comment