በሱዳን እየተካሄደ ያለው ደም አፋሳሽ ግጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት ይገኛል። በጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር እና አጋሮቹ ካርቱምን እና ኡምዱርማንን መልሰው ከተቆጣጠሩበት ጊዜ ጀምሮ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈፀሙት ዘግናኝ የጦር ወንጀልና አካል ማጎደል መረጃዎች ይፋ መሆናቸውን ቀጥለዋል።
እንደ ‘አፍሪካን ዲፌንስ ፎረም’፣ ‘ሁማን ራይትስ ዎች’ እና ‘ሱዳን ዋር ሞኒተር’ ያሉ ተቋማት ባወጧቸው ዘገባዎች መሰረት በሲቪሎች ላይ የተፈጸሙት ድርጊቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ስጋትና ቁጣን ጭረዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጩ ቪዲዮዎች እንደታየው፣ የጦር ሰራዊቱ አባላት የተማረኩ ሰዎችን ወደ ጉድጓድ እየጎተቱ በመውሰድ ረሽነው አንገታቸውን በቢላዋ ሲቆርጡ ታይተዋል። በተጨማሪም ከሱዳን ጦር ጋር የተሰለፉ ቡድኖች በድብደባ የተገደለን ሰው የሰውነት ክፍል ሲበሉ የሚያሳዩ ኢ-ሰብአዊ ምስሎች ይፋ ሆነዋል። እነዚህ አስቃቂ ድርጊቶች ጦሩ ቀደም ሲል በፈጣን ደጋፊ ኃይሎች (RSF) ስር የነበሩ አካባቢዎችን መልሶ ሲቆጣጠር የፈጸማቸው የጦር ወንጀሎች አካል መሆናቸው ተረጋግጧል።
ጥቃቱ በተለይ በብሔር ማንነት ላይ ያተኮረ መስመር መያዙን መረጃዎች ያመላክታሉ። የዳርፉር፣ የኑባ እና የደቡብ ሱዳን ተወላጆች “ከተቃዋሚዎች ጋር ትተባበራላችሁ” በሚል አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት የተረሸኑ ሲሆን፣ በጃዚራ ግዛት ዋና ከተማ ዋድ ማዳኒ ብቻ ቢያንስ 200 የካናቢ ጎሳ ተወላጆችና የደቡብ ሱዳን ዜጎች ተገድለዋል።
በተጨማሪም ህፃናት የሚመስሉ እስረኞችን አይናቸውን አስሮ ወደ ጉድጓድ በመጣል መረሸን እና የሟቾችን አካል አጎድሎ ወደ ቦይ መጣል የተስፋፋ ልማድ ሆኗል።
የሱዳን ጦር ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ተመሳሳይ አሰቃቂ ድርጊቶችን መርምሮ እርምጃ እንደሚወስድ ቢገልጽም፣ እስከ አሁን ግን በቁጥጥር ስር የዋለ ወይም ይፋ የተደረገ የቅጣት እርምጃ የለም። በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩት ምስሎችና ቪዲዮዎች በቦታው ከተፈጸሙት እጅግ አሰቃቂ ድርጊቶች በጥቂቱ ብቻ እንደሆኑ ይታመናል። ይባስ ብሎም በህዝብ በተጨናነቁ አካባቢዎችና ቡና ቤቶች ፊት ለፊት የሲቪል ልብስ የለበሱ ንጹሃንን ያለ ፍርድ የመረሸን ድርጊት በሰፊው ቀጥሏል።
በሌላ በኩል በሰሜን፣ ደቡብ እና ምዕራብ ኮርዶፋን ግዛቶች የድሮን ጥቃቶችና የብሔር ጥቃቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል። በኤል ኦቤይድ እና ሸርሻር መንደሮች በተሰነዘሩ የአየር ጥቃቶች በሴቶችና ህፃናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ በጃብራ አል-ሼክ አካባቢ ደግሞ የከባቢሽ ጎሳ መሪ የሆኑትን ሼክ አዋደላህ አብደላን ጨምሮ 18 ሰዎች በታጣቂዎች ተገድለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (OCHA) እንደገለጸው በእነዚህ ቀጣናዎች በሲቪሎች ላይ የሚደርሰው መፈናቀልና ሰብአዊ ውድመት አሁንም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል።