#Fastmereja:-ከፍተኛ የሕክምና አገልግሎት ፍለጋ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ እና የእስያ ሀገራት የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ታካሚዎችን እንግልት እና ከፍተኛ ወጪ ለማስቀረት ዝግጁ መሆኑን በኬንያ ናይሮቢ የሚገኘው አጋ ካን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል (Aga Khan University Hospital, Nairobi) አስታወቀ።
ሆስፒታሉ ይህንን የገለጸው በዛሬዉ እለት በአዲስ አበባ ከሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር ባካሄደው የምክክርና የጋዜጣዊ መግለጫ መድረክ ላይ ነው።
የአጋ ካን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ራሺድ ካላኒ እንደገለፁት በርካታ አፍሪካውያን ታካሚዎች ለልብ፣ ለካንሰር፣ ለነርቭ እና ለሌሎች ውስብስብ ሕክምናዎች ወደ አውሮፓ፣ ህንድ እና ቱርክ በሚጓዙበት ወቅት ለከፍተኛ የገንዘብ ወጪ፣ ለአካል እና ለሥነ-ልቦና እንግልት እንደሚዳረጉ ገልፀዉ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በጎረቤት ሀገር ኬንያ የሚገኘው አጋ ካን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ዘመናዊ የሕክምና ቴክኖሎጂዎችን እና የካበተ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች በማደራጀት ለአካባቢው ሀገራት ታካሚዎች አስተማማኝ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ተቋሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የJoint Commission International (JCI) የጥራት እውቅና ያገኘ ሲሆን፣ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የሮቦቲክ ኦፕሬሽን ሕክምና እና የ PET Scan/Cyclotron የካንሰር መመርመሪያ ቴክኖሎጂዎችን ስራ ላይ ማዋሉ ተገልጿል።
ከሕክምና አገልግሎቱ ጎን ለጎን ሆስፒታሉ ከኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በስልጠና እና በምርምር አብሮ ለመስራት ማቀዱን አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ስፔሻሊስት ዶክተሮች ወደ ሩቅ ሀገራት ሳይጓዙ በናይሮቢ ከ2 እስከ 3 ዓመታት የሚቆይ የላቀ የስፔሻሊቲ ስልጠና (Fellowship) የሚያገኙበት ዕድል እንደሚመቻች ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ለታካሚዎች ክፍያዎችን ለማቃለል የዶላር፣ ዩሮ እና ዲርሃም ክፍያዎችን በቀጥታ የሚቀበል ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ የሕክምና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋርም አብሮ ለመስራት እቅድ እንዳለው ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት አፍሪካ የዓለምን 25 በመቶ የሕመም ሸክም ብትሸከምም በክሊኒካል ምርምሮች ያላት ድርሻ ከ4 በመቶ በታች መሆኑን የጠቀሱት የሆስፒታሉ ተወካዮች፣ አህጉራዊ አጋርነትን (South-South Partnerships) በማጠናከር በሕክምና ዘርፍ እራስን መቻል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
እ.ኤ.አ. በ1958 የመጀመርያ ደረጃ የሕክምና መስጫ ተቋም ሆኖ የተመሠረተው የአጋ ካን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ናይሮቢ፣ በ2005 የኢጋ ካን ዩኒቨርሲቲ አካል በመሆን በምስራቅ አፍሪካ ወደሚገኝ መሪ የከፍተኛ ደረጃ ማስተማሪያ ሆስፒታልነት የተሸጋገረ ሲሆን በናይሮቢ በሚገኘው ባለ 300 አልጋ ዋና ሆስፒታሉ እና በኬንያና ኡጋንዳ ባሉ 54 የሕክምና ማዕከሎቹ አማካኝነት በዓመት ከ700,000 በላይ ታካሚዎችን ያስተናግዳል።
📷ከበደ መክብብ




