banner

መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን የተቀላቀለ የመጀመሪያው ተቋም ሆነ!

#Fastmereja:-መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ አክሲዮን ማህበር በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዘንድ ህጋዊ ምዝገባውን በስኬት በማጠናቀቅ፣ በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ ታሪክ ውስጥ የመመዝገብ እድል ያገኘ የመጀመሪያው የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም መሆኑን በዛሬዉ እለት በተሰጠ መግለጫ ይፋ ተደርጓል።

ይህ ስኬት ለመባዕ ማይክሮ ፋይናንስ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው የሀገሪቱ የማይክሮ ፋይናንስ ዘርፍ አዲስና ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ገልፀዋል።

በዚሁ የምስራች ማበሰሪያ መርሃ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ማኅበር እና የፈርስት አዲስ ኢንቨስትመንት ባንክ ተወካዮች፣ የተቋሙ የቦርድ አባላት እንዲሁም የፋይናንስ ዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያ አጠቃላይ የፋይናንስ ስርዓቷን በማዘመን እና የካፒታል ገበያን በመክፈት ላይ በምትገኝበት በዚህ ወሳኝ ወቅት መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ የግንባር ቀደምትነት ሚናውን ተወጥቷል ሲሉ ገልፀዋል።

ይህ ህጋዊ ምዝገባም ተቋሙ በካፒታል ገበያው የሚጠየቁትን የህግ፣ የፋይናንስ፣ የኮርፖሬት ገቨርናንስ እና የግልፅነት መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ ማሟላቱን የሚያረጋግጥ እንደሆነ አስረድተዋል።

ይህ ምዝገባ በካፒታል ገበያው በኩል ተጨማሪ ኢንቨስትመንት በመሳብ የፋይናንስ አቅሙን የሚያጠናክርለት ሲሆን፣ ይህም በከተማና በገጠር የሚገኙ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን፣ አነስተኛ አምራቾችንና የህብረተሰብ ክፍሎችን በስፋትና በጥራት ተዳራሽ ለማድረግ እንደሚያስችለዉ ነዉ የተገለፀዉ።

በተጨማሪም ተቋሙ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ቁጥጥር ስር መሆኑ ለባለአክሲዮኖች፣ ለደንበኞች እና ለቁጠባ ባለቤቶች የበለጠ አስተማማኝነትን፣ ግልፅነትንና ሙሉ ዋስትናን የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት በአምስት ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ተቋሙ፣ በብድር አሰጣጥና በቁጠባ አሰባሰብ ዘርፍ አበረታች ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ የቅርንጫፍ ተደራሽነቱን ይበልጥ ለማስፋፋት እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶቹን በፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ እቅድ የያዘ ሲሆን፣ አዳዲስ አክሲዮኖችንም ለነባር እና ለአዳዲስ ኢንቨስተሮች በይፋ ማቅረቡን በመግለፅ ባለሀብቶች ተቋሙን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀርቧል።





Leave a Comment